በተወሰኑ የሀይል ማመንጫ ግድቦች ያጋጠመው የውሃ እጥረት የመብራት መቆራረጥ መንስኤ ነው ተባለ፡፡

ከሰሞኑ በተደጋጋሚ የሚስተዋለው የመብራት መቆራረጥ መንስኤ የሀይል እጥረት ነው ተባለ፡፡በተወሰኑ የሀይል ማመንጫ ግድቦች ያጋጠመው የውሃ እጥረት ግድቦቹ ሀይል እንዳያመነጩ እክል ፈጥሯል ተብሏል፡፡የውሃ እጥረት ያጋጠመባቸው ግድቦች በቂ ውሃ እስኪያገኙ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በፈረቃ የሚሆንበት አሰራር መጀመሩ ተነግሯል፡፡የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የግልገል ጊቤ 3፣ የቆቃና የመልካ ዋከና ሀይል ማመንጫ ግድቦች በበልግ ወቅት ማግኘት የሚገባቸውን ዝናብ ስላላገኙ የውሃ እጥረት አጋጥሟቸዋል፡፡

Related image

ለአገሪቱ ከፍተኛውን ሀይል የሚያመነጨው የግልገል ግቢ 3 ግድብ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የውሃ ከፍታው በ15 ሜትር ዝቅ እንዳለ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ ተናግረዋል፡፡ይህም በሙሉ አቅሙ የሚያመነጨውን 1 ሺ 800 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል እንዳያመነጭ አድርጎታል ብለዋል፡፡የውሃ እጥረት ያጋጠማቸው ግድቦች በውሃ ሞልተው ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ እስኪገቡም መብራት በፈረቃ ማሰራጨት እንደ ዋነኛ አማራጭ መወሰዱ በመግለጫው ተነግሯል፡፡

በተለይም ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች በወጣላቸው ተራ መሰረት እንዲያመርቱ ይደረጋል ተብሏል፡፡የሲሚንቶ ፋብሪካዎች 15 ቀናት እያመረቱ ለ15 ቀናት ማምረት እንዲያቆሙ፣ የብረታ ብረት አምራቾች ደግሞ በ24 ሰዓቱ በወጣላቸው ተራ መሰረት ይሰራሉ ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ የኤሌክትክ አቅርቦቱ በቀን በ3 ምዕራፎች ተከፍሎ እንደሚሰራጭ ተናግረዋል፡፡ካለፈው ግንቦት 1 ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል የተባለው የኤሌክትሪክ የፈረቃ ስርጭት ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ 5 ሰዓት፣ ከ5 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት እና ከ10 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ባሉት ጊዜያት በ3 ምዕራፍ እንደተከፋፈለ አቶ ሽፈራው ተናግረዋል፡፡

ወደ ውጪ አገራት የሚላከውን የኤሌክትሪክ ሀይል መቀነስም ለሀይል መቆራረጡ ሌላኛው መፍትሄ መሆኑን ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ አንስተዋል፡፡በዚህም መሰረት ወደ ሱዳን የሚላከው ሀይል ሙሉ በሙሉ ሊቋረጥ የሚችልበት ሁኔታ አለ ብለዋል፡፡

SHEGER FM 102.1 RADIO