የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነው ተባለ

ከአማራ ክልል፣ ከኦሮሚያ ምስራቅ ወለጋ ዞኖችና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሼና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር፥ በምስራቅ ወለጋ ዞን የተጠለሉ ከ69 ሺህ በላይ ዜጎችን በሳምንቱ መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ወደ መጡበት ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ በቀለ ገልጸዋል።

ተፈናቃዮቹ ወደ መጡበት ሲመለሱም በመኸር እርሻ እንዲሳተፉ ለማድረግ የሚያስችል ድጋፍ፥ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመሆን ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓልም ብለዋል።

በሌላ በኩል በአማራ ክልል ማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተጠልለው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑም ተገልጿል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የአደጋ መከላከል ጽህፈት ቤት ተወካይና የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ አብደላ ኑር፥ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው ተመልሰው የእርሻ ስራቸውን ማከናወን እንዲችሉ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የወደሙ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባትም እስካሁን ከ17 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮችን ወደ ሁለቱም አካባቢዎች መመለስ ተችሏል ብለዋል።

በአካባቢዎቹ በነበረው የፀጥታ ችግር የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባርም እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

በአካባቢዎቹ ዳግም የጸጥታ ችግር እንዳይከሰትም እየተከናወኑ ያሉ የህዝብ ለህዝብ የሰላም መድረኮችም ቀጣይነት እንደሚኖራቸው ሃላፊዎቹ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE