ዴኢህዴን በዎላይታ ሕዝብ ጥያቄ ላይ የመደራደር ሕጋዊ መብትም ሆነ ሞራል የለውም! – የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዎብን)

ግንቦት 09 ቀን 2011 ዓ.ም በዎላይታ ሶዶ ከተማ የተጠራውን ሕዝባዊ ሰልፍ አስመልክቶ ከዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዎብን) የተሰጠ የአቋም መግለጫ!

የዎላይታ ሕዝብ ወደ ዘመናዊት ኢትዮጵያ በኃይል ከተቀላቀለበት ከዛሬ 130 ዓመት ጀምሮ የተፈራረቁ ገዥዎች እንደ ሕዝብ ያደረሱበትን ታሪካዊ እና ነባራዊ መዋቅራዊ ኢፍትሃዊነቶችን አምሮ ሲታገል ቆይቷል:: ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ እየከፋ የመጣውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ብደሎችን በሰላማዊ መንገድ አደባባይ ወጥቶ ለማሰማት ተደጋጋሚ ጥያቄ ለዞኑ መንግስት አቅርቧል:: የዞኑ መንግስትም ከሕዝቡ በተደረገው ከፍተኛ ግፊት እና ጫና በመጭው አርብ ግንቦት 09 ቀን 2011 ዓ.ም ከጥዋቱ 12:00-4:00 ድረስ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ እውቅና ሰጥቷል::

በዚሁ መሠረት የዎላይታ ህዝብ በሰልፉ ላይ በመገፕት የሚከተሉትን የራሱን መሠረታዊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥያቄዎችን የሚያንጸባርቁ መፈክሮችን በነጻነት፣ በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ እንዲያሰማ ዎብን ጥሪውን ያቀርባል::

1. የዎላይታ ሕዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ እና ሕገመንግስታዊ መብት ለድርድር አይቀርብም!

2. በዎላይታ ተዎላጆች ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ አሰቃቂ ግድያ፣ ማፈናቀል እና የንብረት ዘረፋ ያቀነባበሩ እና የፈጸሙ ወንጀለኞች ለፍትህ ይቅረቡልን!

3. መንግስት በሀገሪቷ ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በአስቸኳይ ያስቁም! ድርጊቱን ያስተባበሩትና የፈፀሙ ቡድኖችና ግለሰቦች ለህግ ይቅረቡ!

4. የሀገርም ሆነ የለውጡ ባለቤቶች ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸው! ለውጡ የህግ የበላይነትን፣ ሰብዓዊ ክብርና ዕኩልነትን ያማከለ ይሁን!

5. ዴኢህዴን በዎላይታ ሕዝብ ጥያቄ ላይ የመደራደር ሕጋዊ መብትም ሆነ ሞራል የለውም!

6. መንግስት ለዎላይታ ሕዝብ ፍትሃዊ የመልማት ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ይስጥ!

7. የዎላይታ ሕዝብ ክብርና ህልውና መረጋገጥ ለኢትዮጵያ አንድነት ዋስትና እንጂ አደጋ አይደለም!

8. ሚሊዮኖች የሚናገሩት ዎላይትኛ ቋንቋ በአስቸኳይ በፌዴራል እና በክልል መንግስታት የሥራ እና የመገናኛ ብዙሃን አገልግሎት ላይ ይዋል!

9. ደኢህዴን የዎላይታ ሕዝብን በጎሳ እና በኃይማኖት በመከፋፈል የሚፈጽመው አስተዳደራዊ በደል እና ኢፍትሃዊነት በአስቸኳይ ያቁም!

10. በዎላይታ ሕዝብ እና በአጎራባች ህዝቦች መካከል በደኢህዴን የተዘራው የጥላቻ እና የያለመተማመን አረም ይነቀላል!

የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ
ግንቦት 07 ቀን 2011 ዓ.ም
ዎላይታ ሶዶ


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE