በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ተፈጥሮ የነበረው ረብሻ ተረጋጋ

SHEGER FM 102.1 RADIO

በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ተፈጥሮ የነበረው ረብሻ እየተረጋጋ መሆኑን ዩኒቨርስቲው ለሸገር ተናገረ፡፡

ችግሩን በእርቅና በመግባባት ለመፍታትም ከተማሪዎች ጋር ንግግር ማድረግ መጀመሩን ሰምተናል፡፡

ሸገር ከዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹ እንደሰማው ከዚህ ቀደም የተለያዩ የቀድሞ የአገር መሪዎችን፣ የአክቲቪስቶችን እና ምንም ዓይነት የባንዲራ ምስል የታተመበትን ቲሸርት በግቢው ውስጥ ለብሶ መንቀሳቀስ ተከልክሏል፡፡

ይህም የሆነው ምስሎቹ በታተሙባቸው ቲሸርቶች መነሻነት ፀብ ይነሳ ስለነበር ነው ብለዋል ተማሪዎቹ፡፡

ከትናንት በስቲያ ግን እንዳይለብሱ የተከለከለውን የባንዲራ ምስል ያለበትን ቲሸርት ለብሰው ወደ ግቢ እንገባለን ያሉ የተወሰኑ ተማሪዎች ከግቢው የፀጥታ አካላት ጋር ተጋጭተዋል፡፡

በዚሀም መነሻ ረብሻ ተነስቶ በድንጋይ የመፈንከት አደጋ የደረሰባቸውና ሆስፒታል የገቡ ተማሪዎች እንዳሉ ሰምተናል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ መቅደስ ካሳሁን በበኩላቸው የፀቡ መነሻ ተማሪዎች ያሉት መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ተማሪዎች እርስ በርስ እንዳይጋጩ መሰረታዊ ችግሩን ለማወቅና እርቅ ለማውረድ ዛሬ ከተማሪዎቹ ጋር ዩኒቨርስቲው እየመከረ መሆኑን ነግረውናል፡፡

በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የተቋረጠው የመማር ማስተማር ሂደት ዛሬ የመግባባት ንግግር ከተደረገ በኋላ ይጀመራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ወይዘሮ መቅደስ ለሸገር ተናግረዋል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE