የአብጃታ ሀይቅ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየደረቀ ሲሆን በሚቀጥሉት አምስትና ስድስት ዓመታት ሊጠፋ ይችላል ተባለ

EBC

የአብጃታ ሀይቅ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየደረቀ ነው

የአብጃታ ሀይቅ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየደረቀ ሲሆን በሚቀጥሉት አምስትና ስድስት ዓመታት ሊጠፋ ይችላል ተባለ።ከአውሮፓና ከኤሺያ ጭምር ለሚመጡ ስደተኛ ወፎች መጠለያ ሆኖ የሚያገለግለው የአብጃታ ሀይቅ በአስደንጋጭ ሁኔታ እየደረቀ መሆኑን ነው የአብጃታና ሻላ ሀይቆች ብሄራዊ ፓርክ ሃላፊ የገለፁት ።የፓርኩ ሃላፊ አቶ ባንኪ ቡደሞ ለኢዜአ እንደገለፁት ሃይቁ ከአሁን በፊት 194 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት የነበረው ሲሆንአሁን ከ80 ካሬ ኪሎ ሜትር በታች ሆኗል።

“ጥልቀቱም ከ14 ሜትር ወደ 2 ሜትር ዝቅ ማለቱን ሃላፊው ገልፀው፤ በሚቀጥሉት አምስት ወይም ስድስት ዓመታት ሙሉ በሙሉ ልናጣው እንችላለን” ሲሉ ስጋታቸውን ጠቁመዋል።
“ለሀይቁ በዚህ ደረጃ መገኘት የገባር ወንዞች በመስኖ ልማት ጫና ፍሰታቸው መቋረጡ፣ በአካባቢው የሚገኘው የሶዳአሽ ፋብሪካ የሃይቁን ውሃ የሚጠቀም መሆኑና የደን መመናመን ተከትሎ ሃይቁ በደለል መጎዳት ምክንያት ናቸው”ብለዋል።

አበባ አልሚዎች የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጠቀሙ በማድረግ፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማት በስፋት ማከናወን፣ በፓርኩ ውስጥ ያሉ ሰዎች ደን ከመጨፍጨፍ እንዲታቀቡ በማድረግ ሀይቁን መታደግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

የአርሲ ነገሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ አብዶ በበኩላቸው ችግሩ ከአካባቢው አቅም በላይ በመሆኑ የክልሉናየፌዴራል መንግስት የተቀናጀ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

አብጃታ፣ ሻላና ዝዋይ የመሳሰሉ ሃይቆች ከደረቁ የስምጥ ሸሎቆ አካባቢ ለእሳተ ገሞራ ሊጋለጥ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የባቱ ዓሳና ሌሎች የውሃ ውስጥ ህይወት ምርምር ማእከል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ለማ አበራ ተናግረዋል።

በአብጃታና ሻላ ሀይቆች በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ጨምሮ ፍላሚንጎና ፔሊካን የመሳሰሉት 463 የአእዋፍ ዝርያዎች ይገኛሉ ።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE