ከፍተኛ ፍርድ ቤት እነ ጌታቸው አሰፋ መጥሪያ ይሰጣቸው እንጂ ተይዘው ይቅረቡ አላልኩም አለ

ፋና፣ ሸገር እና ጠቅላይ አቃቤ ህግ የዜና ማስተካከያ እንዲያደርጉ ታዘዋል!

Elias Meseret Taye – የከፍተኛው ፍርድ ቤት ያሉ ምንጮች እንደጠቆሙኝ በአቶ ጌታቸው አሰፋ ዙርያ “መጥሪያ ደርሷቸው ተይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጠ” ብለው በስህተት ዘግበው “መጥሪያ ደርሷቸው እንዲቀርቡ ትእዛዝ ተሰጠ” ብለው እስከ ግንቦት 8 ማስተካከያ እንዲያወጡ በፍርድ ቤቱ ትእዛዝ የተላለፈላቸው ፋና ብሮድካስቲንግ፣ ሸገር ኤፍኤም እና ትንሽ ግር በሚል ሁኔታ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ናቸው። እንደተነገረኝ ጠቅላይ አቃቤ ህግ “ተይዘው እንዲቀርቡ ትእዛዝ ተሰጠ” ብሎ የሶሻል ሚድያ ገፁ ላይ መረጃ አውጥቶ ነበር።

ፋና የዜና ማስተካከያውን ከደቂቃዎች በፊት በማውጣት ቀድሶታል!

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በድረገፁ ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓመተ ምህረት “የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ክስ የተመሰረተባቸውና በቁጥጥር ስር ያልዋሉ አራት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች መጥሪያ ደርሷቸው ተይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጠ” የሚል ዘገባ ማውጣቱ ይታወሳል።

ሆኖም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው ትእዛዝ ፍርድ ቤቱ በግልፅ ከሰጠው ትእዛዝ አንፃር ዘገባው ስህተት መሆኑን አስታውቋል።

በመሆኑም “አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ክስ የተመሰረተባቸውና በቁጥጥር ስር ያልዋሉ አራት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በፍርድ ቤቱ መጥሪያ ደርሷቸው እንዲቀርቡ ትእዛዝ ሰጠ” በሚል እንዲስተካከል እንጠይቃለን።ሲል ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም ለተፈጠረው ስህተትም ይቅርታ ጠይቋል።