አቶ ታደሰ ካሳ የፈፀምኩት ወንጀል የለም፤ ጥፋተኛ አይደለሁም፤ በዚህ ወቅት ዋስትና አልጠይቅም አሉ

BBC Amharic

ባህር ዳር ላይ የእነ አቶ በረከትን ክስ እየተመለከተ ያለው ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት አቶ ታደሰ የፈፀምኩት ወንጀል የለም፤ ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።

ይህን ተክትሎም አቶ በረከት ስምኦን የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን ምንም ዓይነት ጥፋት እንዳልፈፀሙ እና እንደማይጠየቁ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

አቶ ታደሰ ካሳ የእምነት ክህደት ቃላቸውን በቀጣይ ቀጠሮ ለመስጠት መጠየቃቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ጉዳዩን ተመልክቷል።

የሶስተኛ ተከሳሽ አቶ ዳንኤል ግዛው ጠበቃ በበኩላቸው የእምነት ክህደት ቃላቸውን አሻሽለው አቅርበው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርም ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄ ማንሳት እንደሚቻል በገለፀው መሰረት አቶ በረከት ጠበቃ አማክረው እንዲጠይቁ ፍርድ ቤቱ ለሚያቀርቧቸው ጠበቆች ጥበቃ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ዋስትና በሚያስከለክል ወንጀል በመከሰሳቸው ዋስትና ለመጠይቅ እንዲችሉ ክሱ ሊሻሻል እንደሚገባው የጠቀሱት አቶ ታደሰ በዚህ ወቅት ዋስትና አልጠይቅም ብለዋል።

አቃቤ ህግ በበኩሉ ክሱ ዋስትና የሚከለክል መሆኑን ጠቅሶ ጠበቃ ማቆም መብታችው መሆኑን አስታውቋል።

አቶ በረከት “ጠበቃ ለማቆም ሞክረን በደርሰባቸው ዛቻ ምክንያት ሊቆሙልን አልቻሉም” ሲሉ ተናግረዋል።

“ክልሉ ህግ የማስከበር አቅም አጥቷል፤ በጠበቃ የመከራከር መብቴን የሚጋፉት በህግ ይጠየቁ፤ ማረሚያ ቤት እና ፍርድ ቤት እሰደባለሁ፤ ህግ አለ እዚህ ክልል? ሕገ-መንግሥቱ ይከበራል? ከፍተኛ ሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመብኝ ነው፤ ይህ የፍትህ መጨናገፍ ነው” ብለዋል።

አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ

አቶ ታደሰ በበኩላቸው ጠበቆች በሚደርስባቸው ዛቻ ምክንያት አልቆሙልንም፤ ጥበቃ ይደረግላቸዋል፤ ቢባልም ምንም አልተከናወንም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል።

ግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤት ክሱ የዋስትና መብት የማያሰጥ በመሆኑ ተከሳሾች ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው ይከታተሉ ብሏል።

ፍርድ ቤቱ አክሎም ጠበቆችን ለይተው ሲያቀርቡ ስለሚደረግላቸው ጥበቃ ይወስናል በማለት አንደኛ እና ሁለተኛ ተከሳሽ ከቀጠሮ በፊት ለይተው ያሳውቁ ብሏል።

የምስክሮችን ቃል ለመስማት ፍርድ ቤቱ ለግንቦት 21 ቀጠሮ ሰጥቷል። መገናኛ ብዙሃን በችሎቱ አዘጋገብ ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ፍርድ ቤቱ ገልጿል።

አቃቤ ህግ በአቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ ላይ አራት ክሶችን መመስረቱ ይታወቃል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE