ተፈናቃዮችን ይዞ ዕርዳታ መሰብሰቢያና የገንዘብ ማግኛ አድርገው የሚሠሩ አሉ – አቶ ንጉሡ ጥላሁን

Reporter Amharic

በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሐሙስ ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፣ በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ተፈናቃዮች መሀል ግጭቶችን በመቀስቀስና ተራ አሉባልታ በማስነገር ብሎም ያልተነገረን ነገር አጋኖ በማሰራጨት ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ የሚያደርጉና እነርሱን የገቢ ምንጭ የሚያደርጉ እንዳሉ አስታወቁ፡፡

‹‹ተፈናቃዮችን ይዞ ዕርዳታ መሰብሰቢያና የገንዘብ ማግኛ አድርገው የሚሠሩ አሉ፤›› ያሉት አቶ ንጉሡ፣ ኅብረተሰቡ ሥጋት እንዲያድርበትና መተማን እንዳይኖር የማድረግ ድርጊቶች ይከናወናሉ ሲሉም አስረድተዋል፡፡ በዚህም የሕግ የበላይነትን የሚፈታተኑ ጉዳዮች ሲስተዋሉ ቆይተዋል ብለዋል፡፡

ቀጣዩ ወቅት የዝናብ በመሆኑና ያልተጠበቁ በሽታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በማሰብ የ5.2 ቢሊዮን ብር መድኃኒት ግዥ እየተፈጸመ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ንጉሡ፣ ይኼ ጊዜያዊ ድጋፍ ነው ብለዋል፡፡ ዋናው ተፈናቃዮችን ወደ ተፈናቀሉበት ቀዬ መመለስ፣ የሚመለሱበት ሥፍራ ለኑሮ ምቹና ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ ላይ ተተኩሮ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

እስካሁን 875,329 ዜጎች ወደ ነበሩበት ተመልሰዋል ያሉ ሲሆን፣ ይኼም ዓለም አቀፉ አሠራርን በተከተለ መንገድ እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

ግጭቶችና መፈናቅሎቹ የሚያጋጥሙት በማንነት ላይ ተመሥርተው መሆኑን፣ ጥላቻን የያዙ ብሎም በወሰን ጥያቄዎች ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው መፍትሔ ለማበጀት ከባድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE