የአሰሪ እና ሰራተኛ ጉዞ የፎረንሲክ ምርመራ አገልግሎት በድጋሚ ስራ ጀመረ

ለ5 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የአሰሪ እና ሰራተኛ ጉዞ የፎረንሲክ ምርመራ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ አገልግሎቱን ከዛሬ ሚያዚያ 14 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ መስጠት መጀመሩን አስታውቋል፡፡

አገልግሎቱ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት ተቋርጦ የነበረው የአሰሪ እና ሰራተኛ ጉዞ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የጋራ ስምምነት ለመጀመር ያስቻለ መሆኑን የኮሚሽኑ ህዝብ ግንኙነት አመልክቷል፡፡

ወደ መካከለኛው ምስራቅ የስራ ስምሪት ስምምነት ወደ ተደረገባቸው 3 አገራት ማለትም ሳውዲ አረቢያ፤ዮርዳኖስና ኳታር የሚሄዱ ተገልጋዮችን ተቀብለው እያስተናገዱ መሆናቸውን በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ የፎረንሲክ ምርመራ ዳይሬክቶሬት የአሻራ ምርመራ ዲቪዥን ኃላፊው ኮማንደር ተፈሪ አርጋው ገልፀዋል፡፡

ተገልጋዮች ወደ አሻራ ምርመራ ሲመጡ የታደሰ ፓስፖርት፤የህጋዊ ኤጀንሲ ደብዳቤ፤ሁለት ጉርድ ፎቶ ግራፍ እና አስር የኢትዮጵያ ብር በመያዝ በስራ ሰዓት መስተናገድ የሚችሉ መሆኑን ኮማንደር ተፈሪ ተናግረዋል፡፡

ምንጭ፡- የፈደራል ፖሊስ ኮሚሽን