በስደት ላለው ሲኖዶስ ከቀሲስ አስተርአየ ጽጌ የተላለፈ መልዕክት

እፌኑ ለክሙ ዛተ ጦማረ “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ” በአትህቶ ርእስየ እንዘ እትሜነይ “አምላክነ ከመ ይዕቀባ ለዛቲ ሃይማኖት ርትዕት ዲበ ዛቲ ኰኵሕ ዘእንበለ ኅልፈት፡ እስከ ፍጻሜሃ ለዛቲ ዓለም ከመ ተሀሉ እንዘ ትገብር  ባቲ በቃለ ጽድቅ  ዘከመ ቀኖናሃ ለቤተ ክርስቲያን  ወምክረ ተአማንያን በንባብ ርትዕት እንተ ኢኮነት ርስሕት”

ይህች ጽሁፍ አድራሻዋ በውጭ ላለው ሲኖዶስ ቢሆንም፤ በቤተ ክርስቲያናችን የተጠመቀ ገለልተኛ ነኝ የሚለውንም ሁሉ ይመለከተዋልና ለሁሉም ትድረሰው።

ወያኔ ኢትዮጵያን በታትኖ ለማጥፋት በዘረጋው መመሪያ መንቀሳቀስ ጀምሮ ኢትዮጵያን በተቆጣጠረበት ዘመን ዓላማው አድርጎ እስካሁ ያለው፤ በመጀመሪያ የጥቃት ተቀዳሚ ዓላመው አድርጎ የተነሳባቸውን እስካሁንም ያላረፈላቸውን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንና አማራውን ህብረተ ሰብ እንደሆነ ራሱ ወያኔ ደጋግሞ የተነገረውና እየፈጸመ ያለው ምስክር ነው።

ወያኔ እየነጣጠለ ሁሉንም ተራ በተራ ለማጥቃት በዘረጋው እቅዱ፤ “ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንዳትኖር የሚያደርግና፤ አማራውም መጥፋት አለበት ብሎ የተነሳውን የኦሮሞውን ህብረተ ሰብ ባይነ ቁራኛ ተመልከቱት” እያለ  ከዘመተበት ከራሱ ከኦሮሞው ጉያ ቄሮወች “ኢትዮጵያውን ነን” እያሉ ብቅ ሲሉ፤ በጎንደር ያሉ አማሮችም “ኦሮሞው የሥጋየ ክፍያ ያጥንቴ ፍላጭና ደሜ ነውና ሲነካ ያመናል” ሲል የወያኔ ቀልብ ተገፈፈ። በውጭ የሚኖሩ ዜጎችም  ከሀሩርና ከቁር ጋራ እየታገሉ፤ እየታሰሩ እየተፈቱ ሳያሰልሱ የፈጸሙት ተጋድሎ ተደምሮ አቶ ለማ መገርሳን ከወያኔ ሰንሰለት አላቆ በማስፈንጠር “ኢትዮጵያ ማለት ሱስ ነው” እያሉ በመላ ኢትዮጵያውያን ፊት እንዲቆሙ አደረጋቸው። የወያኔ ጥላውም ቆዳውም ተገፈፈ። ዶ ክተር ዓቢይ መሀመድ ደግሞ “ኢትዮጵያ በረዥም ታሪኳ የደመረችን፤ ስንኖር ኢትዮጵያውያን ስንሞት ኢትዮጵያውያን ነን” እያለ ብቅ ሲል ወያኔወችን የቆሙባት መሬት  ከዳቸው።

የዶክተር ዓቢይ ቃል ወደ ተግባር ተቀይሮ፤ ወያኔወች ገዳማቱንና ህዝቡን የሚሰብሩበትን መዶሻ ጥለው፤ ከህዝቡ መካከል ወጥተው የበታተኑት ወገኖች ሁሉ ወደነበረበት ተመልሰውና  ተረጋግተው መኖር እስኪጀምሩ፤ የዶ ክተረ ዓቢይ ቃል ብቻ የተሰበረውን አይጠግንም። የቆሰለውንም አይፈውስም። እንዲያውም፦ህመም  በማስታገስ ብቻ ህዝቡን እያንቀላፋ እንዲሞት የሚያደርግ ፈውስ አልባ ክኒን እንዳይሆን እያለ የተሰቃየው ህዝብ በጥርጣሬ እየተመለከተው ነው።

ይህ እንዳለ ሆኖ በደረሰብን ስብራትና በተነሰነሰብን የጥላቻ መርዝ የተጎዳን እኛ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ሀዋርያት የፈጸሙትን  የክርስትና ተቀዳሚ ተግባር መፈጸም እንዳለብን ይህ ወቅት ያስገድደናል። እስካሁን ወያኔዎች በፈጠሩብንና ራሳችንም በምንፈጥራቸው ምክንያቶች ተከፋፍለናል። ብዙወቻችን  በናት ቤተ ክርስቲያን በሚል ስም፤ የቀረነው ደግሞ ከሁሉም የለሁም ገለልተኛ ነኝ በማለት፤ በማወቀም ባለማወቅም መከፋፈሉን ለግል ጥቅም ምንጭ እያደረግን ቆይተናል።

መጀመሪያ የመከፋፈላችን ፈጣሪ የሆነብንን የጋራ ጠላት ወያኔን መቃወም ሲገባን፤ አንዱ ለሌለው ያልሆነ ስም በመስጠት በህዝባችን እና በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የመከራውን ዘመን እንዲራዘም ከወያኔ ጋራ ተባብረናል። ከእንግዲህ ከዚህ በፊት በሄድንበት መንገድ መቀጠል ያለብን አይመስለኝም። ”ንሁር በፍናዊሆሙ። ወንትሉ በአሰሮሙ” የሚለውን የቅዳሴያችንን መመሪያ በመከተል፤ ከግላችን ጥቅም ተላቀን አካሄዳችንን እና አስተሳሰባችን ቀይረን ከአቶ  ዓቢይ አንደበት የምንሰማው የተስፋ ቃል ወደ ተግባር እንዲቀየር ከሚጥሩት ጎን ተሰልፈን ለህዝባችን በሚጠቅመው መንገድ ከመቆም ሌላ አማራጭ የለንም።

ከእንግዲህ ወዲህ ለምንጓዝበት እቅዳችን መመሪያና ምሳሌ ይሆነን ዘንድ በሀዋርያት ዘመን ክርስቲያኖችን የገጠማቸውንና  ሀዋርያትም ችግሩና የፈቱበትን  አዲስ እቅድ መንገድ ለመግለጽ እሞክራለሁ።  የገጠማቸው ችግር “ካልተገረዛችሁ አትድኑም” የሚል ትምህርት በክርስቲያኖች መካከል ተንኮለኞች ሰዎች በመነስነስ ክርስቲያኖችን መረዙ። በዚህ ምክንያት ሀዋርያት ተሰበሰቡ። በስብሳባቸውም ህዝቡ ከተቸገረበት ከግርዛቱ ይልቅ፤ በህብረተ ሰቡ ከፍተኛ አደገኞች የሆኑ አስቼኳይ ውሳኔ የሚጠይቁ  ሌሎች አጣዳፊ ጠንቆችን ተመለከቱ።

”ካልተገረዛችሁ ለትድኑ አትችሉም“ (የሀዋ 15፡1)የሚለው የተሰበሰቡበትን የመነጋገሪያ ነቁጥ  ወደ ኋላ በማዘግየት አንገብጋቢና ቅድሚያ የሚጠይቁትን ከዚህ በታች የተገለጹትን ችግሮች የመነጋገሪያ ነቁጦች አደረጉ።

1ኛ. ለጣዖት የተሰዋ

2ኛ. ከዝሙት መራቅ

3ኛ. ከደም

ሀዋርያት እነዚህን ነቁጦች የመነጋገሪያ ዓበይት ነገሮች አድርገው ከተወያዩ  በኋላ፤ አስፈላጊ ከሆኑት ከነዚህ በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ  እኛና መንፈስቅዱስ ፈቅደናል። ከዚህ ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ”(የሀዋ 15፡29)ብለው ስብሰባውን ዘጉት። እኛም በዚህ ዘመን ላያ ያለን የየግል ፍላጎታችንና ክብራችን ትተን ወያኔወች በፈጠሩብን  ተንኮል የተጓዝንባቸውን የጥፋት መንገዶች ቀይረን፤ በናት ቤተ ክርስቲያን፤ በውጩ ሶኖዶስ ወይም በገለልተኛነት እያሳበብን ከተጓዝንበት መንገድ ወጥተን፤ በህብረት ባንድነት በሰላምና በጤና ህዝቡን ለማገልገል ከሚያስችል ውሳኔ ላይ የሚያደርስ አዲስ የእ ድ ጉባዔ ራሳችን እንድንፈጥር የደወል ድምጽ ይሰማኛል።

እንደሚታወቀው፦ ከዚህ ቀደም ቀውስ በተፈጠረበት ወቅት ሁሉ በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል የተፈጠረው መለያየት ተወግዶ  እርቁ በቀላሉ የሚፈጸም የመሰላቸው በገርነት ሽምግልናውን የጀመሩት አንዳንድ ወገኖች ቢኖሩም፤ በሀዋርያት ዘመን “ካልተገረዛችሁ አትድኑም” እያሉ ያስቸግሩ የነበሩትን የሚመስሉ ሰዎች በመካከል እየገቡ፤ የእርቁን ወሬ ካጋጋሉት በኋላ ሽምግልናው የውሀ ሽታ እየሆነ  በመቅረት ህዝባችን ተስፋ ሲቆርጥ ኖሯል። አሁንም ቢሆን  “ተጎዳን የሚሉ አባቶች ወደ ሞት አፋፍ እየደረሱን ነው፤  ይግቡና ይቀበሩ፤ የቀሩት ደግሞ ቀድሞውንም የነካቸው የለም፤ እንደኛ ወደ አገራቸው ለመግባት ቢፈልጉ የሚከለክላቸው የለም” የሚሉ  ጵጵስናውን እየገዙ የገቡ  አባ ፋኑዔልን ከመሳሰሉ ሰርጎ ገቦች እየተሰማ ነው።

ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ እንደመሰከሩት እነ አባ ፋኑዔል ጵጵስናውን ከህዝብ በሰበሰቡት ሙዳየ ምጿት ገዝተው ቢገቡም፤ ከጉዳት በቀር ለቤተ ክርስቲያንና ለህዝብ ያስከተሉት ጥቅም እንደ ሌለ በሁሉም የታወቀ ነው። የራሳቸውን ሞራለ ብልሹነት ለመሸፈን አቡነ ፋኑዔል ለሚያሰራጩት ሸፍጥ “ያለ በቂ ምክንያት እንደታሰርን ያለ በቂ ምክንያት የምንፈታ ጥጆች አይደለንም” ብለው የወልድባ ገዳም መነኮሳት የተናገሩት ሁሉንም የሚያስተምርና መልስም ይመስለኛል። ለ27 አመታት የተከፈለውን መስዋዕትነት ከንቱ አድርገው፤ ወያኔ የሰራውንም የጥፋት ታሪክ እንዳልተፈጸመ ለማድረግ በህዝቡ መካከል የሚቅበዘበዙትን አሳፍሮ፤ በተለያዩ  ምክንያቶች የተለያየውን  ሁሉ ሳያገል፤ ሁሉንም የሚያካትት መነጋገሪያ ቁም ነገር በመዘርጋት፤ በውጭ ያለው ሲኖዶስ ሁላችንንም እርስ በርሳችን እንድንጠራራ የሚያደርገን ጥሪ ማዘጋጀቱ ፤ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዘላቂ  ጤናማና ጠቃሚ ውጤት ላይ የሚያደርስ ይመስለኛል።

ይህን መሳይ ጥሪ ሲቀርብ፤ መለያየቱን የግል ጥቅምና ክብር ምንጭ አድርገው ለመኖር የወሰኑ ሰዎች ሊቃወሙና ሊያጉረመርሙ መሞከራቸው እንደማይቀር መገመት አያዳግትም። ሆኖም በዚህ መንገድ የሚቀርበውን ጥሪ በዚህ ወቅት ላለመቀበል መሞከር፤ በስለት ላይ ቆሞ ራስን ከመጉዳት በቀር፤ አስመሳይ ምክንያት እየፈጠሩ ህዝቡን እንደቀድሞው ለመንዳት መሞከር ከእንግዲህ የሚቻል አይመስለኝም። ከእንግዲህ ”ውሸትን አስወግዳችሁ እርስ በርሳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋራ እውነትን ተነጋገሩ። ተቆጡ። ኃጢአት አታድርጉ። በቁጣችሁ ጸሀይ አይግባ ለዲያብሎስ ፋታ አታስጡት ። የሰረቀ ከእንግዲህ አይስረቅ“ኤፌ 4፡25᎗28የሚለውን ምክር ብቻ መከተሉ የሚጠቅም ይመስለኛል። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እስካሁን ለዲያብሎስ  ፋታ በመስጠት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የፈጸምነው በደል ሊያበቃ ይገባል።እርስ በርስ በመናቆር ባሰለፍናቸው አመታት የፈጸምናቸው በደሎች በየአንዳንዳችን ላይ ካለብን ፤ ሁሉም ተስማምቶ የሚሰይመው የሊቃውንት ጉባዔ እየመረመረ የሚሰነዘረውን ማረሚያ ለመቀበል የተዘጋጀ መንፈስና ድፍረት ሊኖረን ይገባል።  የድፍረት እንጅ የፍርሀት መንፈስ ከእግዚአብሄር አለመቀበላችንን አባቶቻችን ሊቃውንት እንዳስተማሩንና፤ ይህም የቤተ ክርስቲያን ልጅነታችንን ከምንገልጽባቸው መንገዶች አንዱ መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም።

በዚህ ሳምንት በአሜሪካ ዙሪያ በቤተ ክርስቲያናችን ስም የሚካሄደው ዓመታዊ ጉባዔ፤ ሀዋርያት እንዳደረጉት ከተዘራው መከፋፍያ መርዝ ራሱን አላቆ፤ የዚህ፤  የዚያ፤ ወይም ገለልተኛ ሳይል በተለያዩ ምክንያቶች የተበታተነውን ሁሉ መሰብሰብ የሚያስችል ሀዋርያዊ እቅድ በመዘርጋት “ ከነዚህ በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ  እኛና መንፈስቅዱስ ፈቅደናል። ከዚህ ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ”(የሀዋ 15፡29)ብሎ ስብሰባውን መዝጋቱ ለሁሉም የሚጠቅም ይመስለኛል። ከላይ እንዳልኩት እስካሁን ወያኔዎች በፈጠሩብን የመለያያ ችግር በየራሳችንም ድክመት  ጭምር በተበታተነ መንገድ በመሄዳችን መበታተኑ እንደ መልካምም ልማድ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። ይህ አካሄድ ሰይጣን ተንኮለኞችን በመጠቅም ያገባብን ጥፋት እንጅ፤  የጥንታውያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት ትውፊት አይደለም። የጎደለውን በመሙላት የደከመውን እንዲጠነክር ተጽእኖ ለማሳደር ሞከሮ ካልተቻለ ህልውና እንደሌለው በግልጽ አሳውቆ ካልሆነ በቀር እንደሌለ አድርጎ ቆጥሮ በጎድን ጉባዔ ማድረግ የሁለቱንም ሲኖዶሶች ህልውና መካድ ነው። እንደሚታወቀው  በአገራችን ያለው ሲኖዶስ፤ የውጩን ሲኖዶስ ህልውና ተቀብሎ  ሳይሳካ ቢቀርም፤ ለእርቅና ለሰላም ለድርድርም መፍቀዱ አብሮም ኪዳን መሳተፉ የሚዘነጋ  አይደለም። ጉድለትና ድካም አለበት የሚባል ከሆነም ለማስተካከል የጎደለውን እየሞሉ ጥረት ማድረግ እንጅ፤  ሌላ ጉባዔ ማድረግ እስካሁን ከተፈጸመው የከፋ አደጋ መፍጠር መሆኑን  ድምጻችንን ከፍ አድርገን የማሰማት ግዴታ አለብን።

ምእመናንም እስካሁን የተሄደበት መንገድ የሚጎዳና ለጥቂቶች ሰዎች ጥቅም ያገለገለ እንደሆነ በመገንዘብ፤ በጥጋችን ያለው ይህ ሲኖዶስ ከተቀበረበት ሰንጥቆ በመውጣት በአገራችን ውስጥ ባለችውም ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ተጽእኖ እንዲፈጠር የማድረግ ግዴታ እንዳለበት፤ ካልቻለም አለሁ ማለቱን እንዲያቆም ተጽእኖ የማሳደር ግዴታ መብትና ሀይል እንዳላችሁ የማሳሰብ ግዴታየን ለመወጣት ይህችን ጦማር ለምእመናኑም በትህትና አቀርባለሁ።

በተረፈ ተስፋ ቅቡጻን እያልን የምናመሰግነው አምላክ አሁን አገራችን ኢትዮጵያ የደረሰችበትን  የተስፋ ጭላንጭል ስለሰጠን የተመሰገነ ይሁን!

ቡራኬያችሁን እመኛለሁ።

ግንቦት 1 ቀን 2010 ዓ.ም.