በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በሄሌኮፕተር የታገዘ የቁጥጥር ስራ እየተሰራ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ መሆን አልቻለም ተብሏል፡፡

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተነሳው እሳት እስካሁን በቁጥጥር ስር አለመዋሉ ተነገረ፡፡

ከትናንት ጀምሮ በሄሌኮፕተር የታገዘ የቁጥጥር ስራ እየተሰራ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ መሆን አልቻለም ተብሏል፡፡

በቀይ ቀበሮ ጥበቃ ፕሮጀክት የሰሜን ፕሮጀክት አስተባባሪው አቶ ጌታቸው አሰፋ ለሸገር ሲናገሩ ሄሌኮፕተሯ ውሃ ለመቅዳት ወደ ደባርቅ ስትመለስ በሚፈጠረው ክፍተት ያጠፋችው እሳት ተመልሶ የሚቀጣጠልበት የጊዜ ክፍተት እያገኘ ነው ብለዋል፡፡

Image may contain: outdoor

ወደ ቆላማው የፓርኩ ክፍል የወረደው እሳት መጠኑ ከፍ ያለ መሆኑን አቶ ጌታቸው ነግረውናል፡፡

በተለይም ሙጭላ በተባለው የፓርኩ ክፍል ያሉት የግራር፣ የአስታ እና የወይራ ዛፎች በቃጠሎው ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ከባለሙያው ሰምተናል፡፡

ይኸው የፓርኩ ክፍል ዋልያ፣ ድኩላ እና ሌሎች የዱር እንስሳት መኖሪያ መሆኑን የነገሩን አቶ ጌታቸው እንስሳቱ ላይም ከፍተኛ አደጋ ተጋርጧል ብለውናል፡፡

አሁን ላይ እሳቱን በ1 ሄሌኮፕተር ለማጥፋት አስቸጋሪ በመሆኑም ሌላ ተጨማሪ ሄሌኮፕተር ቢገኝ የተሻለ ውጤት ማምጣት ይቻላል ተብሏል፡፡

ካለፈው መጋቢት 30 ጀምሮ በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በድጋሚ የተነሳው እሳት ከ700 ሄክታር በላይ የፓርኩን ክፍል ማቃጠሉን ሰምተናል፡፡

ከኬንያ በተገኘች 1 ሄሌኮፕተር 10 አባላት ያሉት የእስራኤል የእሳት አደጋ ተቆጣጣሪዎች ቡድን በስፍራው ተሰማርቶ እሳቱን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡