ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚጠጉ ዜጎች በተለያዩ ሱሶች መያዛቸው ተገለፀ

Image may contain: 3 people, people sitting

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከጠቅላላ ህዝቦቿ መካከል ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚጠጉ ዜጎቿ በተለያየ አይነት ሱስ የተያዙ መሆናቸው ተገለፀ፡፡

ይህ የተባለውም የፀረ ሱስ ማህበራዊ እንቅስቃሴ መክፈቻ ፕሮግራም “አይሰለጥንብኝም” በሚል መሪ ቃል በይፋ በተጀመረበት መድረክ ላይ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ኢትዮጵያ በለጋና በአፍላ ዕድሜ ክልል ያሉ ወጣትና አምራች ዜጎቿን ወደ አስከፊ ችግር ውስጥ እያስገባ ባለው ሱስና የሱሰኝነት ችግር ላይ ሁሉም ማህበረሰብ ከመንግስት ጎን በመሆን ሊሰራ እንደሚገባ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከኢትዮጵያ ጠቅላላ ህዝቦች ውስጥ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚጠጉ ዜጎች በተለያዩ ሱሶች መያዛቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል ።

በመድረኩ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት የመጡ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

የንቅናቄ ፕሮግራሙ በኢፌዴሪ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮና በአይሰለጥንብኝም ንቅናቄ ፕሮግራም አስተባባሪዎች በቅንጅት የተዘጋጀ ነው።

ንቅናቄው አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

FBC


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE