በደቡብ ክልል የዞን መዋቅር ለውጥ ግጭት 7 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ በሺዎች ተፈናቅለዋል

በደቡብ ክልል፤ የዞን መዋቅር ለውጥ ግጭት እያባባሰ ነው

– እስካሁን “7 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ በሺዎች ተፈናቅለዋል”
– “የዞን አስተዳደሩ ሙሉ በሙሉ ከስራ ውጪ ተደርጓል”
– “መከላከያ ኃይል እንዲገባልን ተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበናል”

Addis Admass
በደቡብ ክልል በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን፣ ጉማይዴ ወረዳ አካባቢ፣ ከዞን መዋቅሩ ጋር በተያያዘ በተከሰተ ግጭት እስካሁን ሰባት ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከ4800 በላይ ሰዎች ደግሞ ከቀዬአቸው መፈናቀላቸው ታውቋል፡፡

Image may contain: one or more people, crowd and outdoorበቅርቡ ለኮንሶ ወረዳ የዞን አስተዳድር መዋቅር ሲሰጠው የሌሎቹ እጣ ፈንታ ባለመወሰኑና የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን አስተዳደር በልዩ ልዩ ሁኔታ ስራውን በአግባቡ እንዲሰራ እድል ያልተሰጠው በመሆኑ፣ በአዲሱ የኮንሶ ዞን አስተዳደርና በቀድሞው የሰገን ህዝቦች ዞን አስተዳደር መካከል ግጭት መቀስቀሱን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል::

የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አማረ ቦሬ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው ካለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር መኖሩን ጠቁመው፤ በስፍራው ለተከሰተው የፀጥታ ችግር መነሻ ምክንያቱ የመዋቅር ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡ ኮንሶ ቀደም ሲል በሰገን ህዝቦች ዞን ስር የሚተዳደር ሆኖ መቆየቱን የገለፁት የዞን አስተዳዳሪው፤ በቅርቡ ኮንሶ ራሱን በዞን መዋቅር እንደሚያስተዳድር ከተወሰነ በኋላ አልፎ አልፎ ግጭቶች ሲቀሰቀሱ መሰንበታቸውን ተናግረዋል፡፡

ኮንሶ የዞን አስተዳደር ሆኖ ሲዋቀር የቀሪዎቹ ወረዳዎች እጣ ፈንታ ባለመታወቁ ምክንያት በአዲሱ የኮንሶ ዞን አስተዳደርና በቀድሞው የዞን አስተዳደሮች መካከል ግጭቱ ተባብሶ በአካባቢው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር መከሰቱን አቶ አማረ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ግጭት ሳቢያ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎችን ቁጥር ለመናገር እቸገራለሁ ያሉት የዞኑ አስተዳዳሪው ከ4810 በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀላቸውንና በንብረትም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ችግሩ ያለበትን ደረጃና በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ የፀጥታ ችግር በመግለፅ፣ ለፌደራል መንግስት ጉዳዩን በተደጋጋሚ ማሳወቃቸውን የገለፁት የዞን አስተዳዳሪው፤ መከላከያ ወደ ስፍራው ገብቶ የአካባቢውን ፀጥታ እንዲያስከብርና የህዝቦችን ህይወት እንዲታደግ ላቀረብነው ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ አላገኘንም፤ በስፍራው ያለው የፀጥታ ችግር ግን ተባብሶ ቀጥሏል ብለዋል፡፡

Image may contain: 1 person, crowd and outdoorበደቡብ ህዝቦች ክልል የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን አስተዳደሩ ካለፈው የካቲት 30 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሽመደመድ ተደርጓል ያሉት የዞን አስተዳዳሪው፤ በአካባቢው የዘርና የማንነት ጉዳይም ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ፣ ፌደራል መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድና እየጠፋ ያለውን የሰው ህይወት እንዲሁም የሚደርሰውን የንብረት ውድመት እንዲታደግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡

ስፍራው በህግና በስርዓት የሚተዳደርና መንግስት ያለበት አገር እንደማይመስል የገለፁት ነዋሪዎች፤ በአካባቢው ችግር እየፈጠሩ ያሉት “የምንተዳደረው በሲዳማ ክልል ነው፤ ደቡብ ክልል እኛን አይወክለንም” የሚሉ ወገኖች ጥያቄ በማንሳት ለፀጥታ ችግሩ መባባስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አካባቢው በከፍተኛ የተኩስ ድምፅ እየተናጠ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዎች፤ በተኩስ ልውውጡም ንፁሃንና ሰላማዊ ዜጎች እየሞቱ ስለሆነ መንግስት ይድረስንል ብለዋል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE