በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተነሳው እሳት ወደ ገደላማው ክፍል እየተዛመተ ነው

በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ የተነሳው እሳት ወደ ገደላማው የፓርኩ ክፍል እየተዛመተ መሆኑን የፓርኩ ስራ አስኪያጅ አቶ አበባው አዛናው ተናገሩ።

ስራ አስኪያጁ በስፍራው ለሚገኘው የጋዜጠኞች ቡድን በሰጡት መግለጫ፥ አሁን ላይ እሳቱ ወደ ገደሉ መስፋፋቱን ተናግረዋል።

በዚህ ሳቢያም የእሳቱን ፍጥነት መቆጣጠር አለመቻሉን ጠቅሰው፥ ለዚህም የአካባቢው ተፈጥሯዊ አቀማመጥና በአካባቢው ያለው ነፋሻማ አየር አስተዋጽኦ ማድረጉንም ነው የተናገሩት።

ከዚህ ባለፈም በየቀኑ በርካታ ቁጥር ያለው ሰው ቢሰማራም የመከላከል ስራው በባለሙያ የተደገፈ አለመሆኑ እና እሳቱን ለመከላከል ለተሰማራው ቡድን የቁሳቁስና መሰል የግብዓት አቅርቦት ከማድረስ አንጻር ያለው ክፍተትም የመቆጣጠር ሂደቱን አዳጋች አድርጎታልም ነው ያሉት።

አሁን ላይ የሚታየውን ክፍተት ለመሸፈንም ከዛሬ ጀምሮ የሚሰሩ አምስት ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል ብለዋል።

እሳት በማጥፋት ልምድ ያላቸውና ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና የተለያዩ ተቋማት የተውጣጣ የቴክኒክ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፥ ይህ ቡድን ቦታውን በማጥናት እሳቱን በምን መልኩ መቆጣጠር ይቻላል የሚለውን አግባብ የሚያሳይ ነው ተብሏል።

ከመንግስትም ሆነ ከተለያዩ አካላት የሚመጣውን ድጋፍ በሰዓቱና በትክክለኛው ጊዜ ቦታው ላይ እንዲደርስ የሚሰራ የግብዓት አቅርቦት ቡድን፣ በፓርኩ ላይ የደረሰውን ውድመትና የደረሰውን ጉዳት በዝርዝር አጥንቶ የሚያቀርብ ቡድን።

የአደጋውን መነሻና በቀጣይ መሰል ስጋቶችን በመለየት የሚከታተልና የሚሰራ ከዞኑ ፖሊስና ከፀጥታ አካላት የተውጣጣ ቡድን እንዲሁም ከጋዜጠኞችና የኪነ ጥበብ ሰዎች የተውጣጣ የመረጃ ግብረ ሃይል ቡድን ተቋቁሟል።

ይህ የመረጃ ግብረ ሃይልም በስፍራው ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ በመመልከትና ከፓርኩ የስራ ሃላፊዎች ጋር በመገናኘት ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝቡ የሚያደርስ ነው።

ስራ አስኪያጁ በመግለጫቸው በደረሰው የእሳት አደጋ ከአይጦችና ከአዕዋፍ ጎጆዎች በስተቀር በትልልቅ አጥቢ እንስሳት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አስረድተዋል።

አሁን ላይም እሳቱን ለማጥፋት በየቀኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው የጸጥታ አካላት፣ የአካባቢው ማህበረሰብና ከተለያዩ ስፍራዎች የመጡ በጎ ፈቃደኞች እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጅ የእሳቱ የመዛመት ፍጥነት ከፍተኛ በመሆኑ ሁኔታውን በሰው ሃይል መቆጣጠር አስቸጋሪ መሆኑንም አንስተዋል።

አሁን ላይ ያለው ነፋሻማ አየርና የእሳቱ የመዛመት ፍጥነት ከሰው አቅም በላይ በመሆኑም መንግስትም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት አስቸኳይ ድጋፍ በማድረግ ፓርኩን ከውድመት ሊታደጉት እንደሚገባም ጥሪ ቀርቧል።

በፓርኩ የሚገኘው የጋዜጠኞች ቡድንም በርካታ ቁጥር ያለው ሰው እሳቱን ለማጥፋት እየተረባረበ ቢሆንም፥ የእሳቱ የመዛመት ፍጥነት ከሰው ቁጥጥር ውጭ መሆኑን መታዘብ ችሏል።

FBC


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE