በባለስልጣናት ነጋዴዎች ተይዞ የነበረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሶማሌ ክልል ሕዝብ ቁጥጥር ስር መግባቱ ተነገረ

በሶማሌ ክልል ዘላቂ ስላምን በማስፈን ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ መሐመድ ተናገሩ።

በሶማሌ ክልል ባለፉት ወራት በርካታ ለውጦች እንዲመጡ መሰራቱን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ መሐመድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

የፈረሱ የመንግስት መዋቅሮችን የማደራጀትና ሰላምና ፀጥታን በማስከበር የህዝቡን ደንህነት ማስጠበቅ ቀዳሚ ትኩረት አግኝቶ ሲሰራበት መቆየቱንም ነው የሚናገሩት።

በዋናነትም በክልሉ ትጥቅን አማራጭ አድርገው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ሀይሎች ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግም ከአጎራባች ክልሎች ጋር ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን ማቃለል ተችሏልም ነው ያሉት ምክትል ርዕስ መስተዳድሩ።

ለውጡን ተከትሎ የክልሉ ህዝብ ያለገደብ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብቱን ተጠቅሞ የማህበራዊ ግንኙነቱን በክልሉ ብቻ ሳይወሰን ከጎረቤት ሃገራት ጋር ትስስሩን አጠናክሯልም ነው ያሉት።

በዚህም በተወሰኑ የክልሉ አመራሮች በበላይነት ተይዞ በቆየው የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች እንዲሳተፉ በር መክፈቱንም አንስተዋል።

የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ሙስና ፈፀመው ወደ ውጭ የወጡ ሰዎችን አሁን ወደ ህግ ማቅረብ ባይቻልም በግጭት ምክንያት ከአካባቢው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቀድሞ ቀያቸው መመለስ ተችሏል ብለዋል።

በሶማሌ ክልል ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጠቀሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ለዚህም ክልሉን የሚመራው ፓርቲ ብቃት ያላቸውን አመራሮች ወደ ፊት እንዲመጡ ማድረጉን ገልጸዋል።

ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ በክልሉ ትግል ሲያካሂድ የቆየው የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ ግንባር / ኦብነግ/ በሃገሪቱ የመጣውን ለውጥ ለመደገፍ መዘጋጀቱን የግንባሩ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሁሴን መሐመድ ኡመር አስረድተዋል።

ሃላፊው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ በሃገሪቱ በርካታ ጊዜያት ለውጥን ተከትሎ የሚታዩ የዴሞክራሲ መሰረቶች ተስፋ ይሰጡ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዋናነትም የዴሞክራሲ ሂደትን መጀመር ብቻ ሳይሆን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ማሸጋገር ይገባል የሚል እምነት አላቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም የሃገሪቱን የፖለቲካ ባህል ለመቀየር ብልሃት በተሞላበት ሁኔታ የሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ ተስፋ እንደሚሰጥም ጠቅሰዋል።

ኦብነግ አሁን በመጣው ለውጥ ወደ ኋላ የሚመልሰው ነገር እንደሌለ በመጥቀስም፥ ግንባሩ አሁን ላይ አስቸኳይ ባይሆንም በሂደት በርካታ ነገሮችን ለመቀየር እየሰራ ነው ብለዋል።

ግንባሩ ከስያሜው ጀምሮ በርካታ ማሻሻያዎችን ለማድረግ በቀጣይ ሳምንት የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በማድረግ በጠቅላላ ጉባኤው እንደሚመክርም አስረድተዋል።

ኦብነግ የፖለቲካ መርሃ ግብሩ፣ ስትራቴጂዎቹና መተዳደሪያ ደንቦቹን በመቀየር የፖለቲካ ፓርቲ ለመሆንም ያለውን እውነታ በማጤን የሃገሪቱን ህግ፣ ስርዓትና ህገ መንግስት እየፈተሸ ነውም ብለዋል በንግግራቸው።

FBC


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE