ፍኖተ ሠላም – በመስኮት ዘሎ ክፍል ውስጥ የገባ ነብር በኮሌጅ ተማሪዎች ላይ ጉዳት አደረሰ

በመስኮት ዘሎ ክፍል ውስጥ የገባ ነብር በተማሪዎች ላይ ጉዳት አደረሰ

በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሠላም ከተማ በፍኖተ ዳሞት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አንድ ነብር በመስኮት ዘሎ ክፍል ውስጥ በመግባት በትምህርት ላይ በነበሩ ተማሪዎች ላይ ጉዳት አድርሷል።

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት 10፡30 ሰዓት ድረስ ጥቃት ፈጻሚው ነብር የኮሌጁን አንድ ብሎክ በቁጥጥሩ ስር እንዳዋለ ነው የተገለፀው።

የኮሌጁ ዲን አቶ ነብዩ መኮንን እንደተናገሩት ዛሬ ጠዋት የኮሌጁ ሰራተኞች አገር አማን ብለው ስራቸውን ጀምረው ነበር።

በድንገት ከየት እንደመጣ ያልታወቀ ነብር በመጀመሪያ የጥበቃ ሰራተኛውን ለመተናኮል ሲሞክር ጥበቃው ያመልጠዋል።

በመቀጠልም ለማስተማር ወደ ክፍል በመጓዝ ላይ የነበረች አስተማሪን ድንገት በማስደንገጡ ትወድቃለች።

ነብሩ ግን በዚህ አላበቃም። ከአንድ የመማሪያ ክፍል በመስኮት ዘሎ በመግባት በክፍሉ ውስጥ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የነበሩ ተማሪዎችን ማራወጥ ያዘ።

ሁሉም በበር ተሯሩጠው ለማምለጥ ቢሞክሩም ወደኋላ የቀሩ ተማሪዎች ላይ ግን ዘሎ ተከመረባቸው።

በዚህም በ2 ተማሪዎች ላይ የመንከስ አደጋ ማድረሱን አቶ ነብዩ ገልጸዋል።

ነብሩ በተለይ በአንደኛው ተማሪ ላይ በአንገቱ፣ በራሱና በእጁ ላይ ጉዳት ማድረሱን የገለፁት አቶ ነብዩ፣ ተጎጂዎች በሆስፒታል ህክምና ተደርጎላቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

ጥቃቱን ያደረሰው አመጸኛ ነብር ግን ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከኮሌጁ የህንጻ ብሎኮች አንዱን ተቆጣጥሮ ቆይቷል፡፡

በዚህም የኮሌጁ ማህበረሰብ አባላት ወደ ህንጻው እንዳይጠጉ መደረጉንም አቶ ነብዩ ገልጸዋል።

ከፖሊስ ጋር በመተባበር ከስራ ሰዓት በኋላ አመሻሽ ላይ ነብሩን ከኮሌጁ ግቢ ለማስወጣት እየሰራን ነው ብለዋል።

ከኮሌጁ የጥበቃ ሰራተኞች በተገኘ መረጃ መሰረት ነብሩ ከዚህ ቀደም አልፎ አልፎ ምሽት ላይ በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ይታይ ነበር፡፡

ምንጭ፡ ኢዜአ


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE