የዜግነት ፖለቲካ ተዳከመ እንጂ አልጠፋም፤ አይጠፋምም በዜግነት ፖለቲካ ላይ ከተሠራ አሸናፊው የዜግነት ፖለቲካ ይሆናል፡፡

‹‹አሁን ያሉት የብሔር የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ዕቅዳቸውን እና ዋነኛ ዓላማቸውን እንኳ በአግባቡ መተንተን አይችሉም፡፡›› ዶክተር ባንተይገኝ ታምራት- የኢዴፓ ምክትል ፕሬዝዳንት

‹‹የዜግነት ፖለቲካ በተንጠልጠል ያለ እንጂ ሕገ-መንግሥቱ የሚያቀነቅነው ብሔርን ነው፡፡ የዜግነት ፖለቲካን በሀገሪቱ ላይ ለማስረጽ ሕገ-መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ መደረግ መቻል አለበት፡፡›› አቶ መልካሙ ሹምዬ- የአብን የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ

‹‹የዜግነት ፖለቲካ ተዳከመ እንጂ አልጠፋም፤ አይጠፋምም፡፡ በዜግነት ፖለቲካ ላይ ከተሠራ አሸናፊው የዜግነት ፖለቲካ ይሆናል፡፡ ›› ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከዘመነ መሳፍንት በመቀጠል ‹‹እኔ አውቃለሁ›› ባይ አካቢቢያዊ ፖለቲከኛ የበዛበት ይህ ዘመን ይመስላል፡፡ እንደ መሳፍንቱ ዘመን የስልጣን ሽኩቻ የበዛበት፣ አካባቢን እንጅ ሀገርን ለመምራት ማሰብ የማይቻልበት የሚመስል የፖለቲካ ተልመጥማጭነት የሚስተዋልበት ጊዜ ላይ ኢትዮጵያ መቆሟን ሁኔታዎች ያሳያሉ፡፡ በዘመነ መሳፍንቱ ‹ባላባቶች› እንደሞከሩት አሁን ደግሞ ‹ብሔር ተኮር› ፓርቲዎች አካባቢን ለማስተዳደር ጥረት እያደረጉ ነው፡፡

በሀገሪቱ የተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢትዮጵያ ብሔሮች ቁጥር በላይ ሆነዋል፡፡ እንዲያውም ለአንዳንድ ብሔሮች ከሦስት በላይ ተወካይ ፓርቲዎች አሏቸው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት ሐሳብ ለመያዝ የተቸገረው ሕዝብ ደግሞ ውዥንበር ውስጥ ገብቷል፤ ክፉ እና ደጉን መለየትም አቅቶታል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜም ኢትዮጵያዊ አንድነት እንደ ወንዝ ዳር መሬት እየተሸረሸረ የብሔር ስሜት እየጎለበተ መምጣቱን የሚናገሩም በዝተዋል፡፡

የመንደር ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በበዙበት ሀገር ውስጥ ሀገራዊ አንድነት ሊያመጡ የሚችሉ ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴት አሸናፊ ሊሆኑ ይችላሉ?

የኢትዮጵያ መጻኢ እድልስ አጣብቂኝ ውስጥ አልገባም?

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ባንተይገኝ ታምራት ‹‹የብሔር የፖለቲካ ፓርቲዎች መበራከት ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው የመጡ በመሆናቸው ተቃውሞ የለኝም፡፡ ኅብረተሰቡ ግን ጠቃሚውን ቆም ብሎ በአስታውሎት መመልከት ይገባዋል›› ብለዋል፡፡ የብሔር ፖለቲካ ችግር እና ብሶት የወለደው በመሆኑ እንደ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ሲታይ ለሀገር ጠቃሚ አለመሆኑንና አሸናፊም እንደማይሆን ዶክተር ባንተይገኝ ይሞግታሉ፡፡

ኅብረ-ብሔራዊነትን ያቀፈ፣ የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን ጥያቄ እና ፍላጎት የያዘ ሀገራዊ ጠንካራ ፓርቲ መመሥረት የሚቻልባቸው ዕድሎች ብዙ እንደሆኑም ዶክተር ባንተይገኝ ተናግረዋል፡፡ ሀገራዊ ፖርቲ በመመሥረት ኢትዮጵያን በአንድነቷ ማስቀጠል እንደሚቻል የሚያረዱት ዶክተር ባንተይገኝ ኢሕአዴግ እንደመንግሥት ሲመሠረት ጀምሮ የመጣው የብሔር ፖለቲካ ሀገራዊ አንድነትን እንደማያረጋገጥ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የዘር ፖለቲካ በበዛ ቁጥር የሕዝቦች አንድነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያመጣ ነው›› ብለዋል፡፡

‹‹አሁን ያሉት የብሔር የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹ከአንዱ ብሔር ለምን እናንሳለን?› የሚል ውድድር ውስጥ የገቡ ናቸው፤ የፖለቲካ ዕቅዳቸውን እና ዋነኛ ዓላማቸውን እንኳ በአግባቡ መተንተን አይችሉም፤ ወጣቱን በመያዝ በስሜት የሚነዱ ናቸው፤ በመሆኑም ኢትዮጵያዊ አንድነትን ያሻክራሉ፤ ይህ በመሆኑ ደግሞ ኢትዮጵያዊ አንድነትን እና ማንነትን ቀንሶ የብሔር ማንነት እንዲጨምር በር ከፍቷል፡፡›› ብለዋል፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት የሚያምን፣ ስለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የሚሰብክ እና ለኢትዮጵያ የሚሞት በመሆኑ ከብሔር ፖለቲካ በተሻለ ሀገራዊ አንድነትን ማምጣት ለሀገሪቱ አስፈላጊ መሆኑንም መክረዋል፡፡

በሀገሪቱ አንድነትን የሚያመጡ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎለብቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲመሠረቱ እና በየመንደሩ የሚመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዲቀንሱ አዲስ ሕግ አርቅቆ ‹ፓርቲ ማለት ምን ማለት ነው? ምንስ ማሟላት አለበት? ተግባሩስ ምንድን ነው?› የሚለውን ማመላከት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡ ‹የመንደር ፖለቲካ በበዛበት ሀገራዊ አንድነት ያላቸው ፓርቲዎች በምን መልኩ አሸናፊ ይሆናሉ?› ለሚለው ጥያቄም ‹‹ሀገራዊ ፓርቲዎች ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሥራዎችን መሥራት አለባቸው፡፡ ሕዝቡም ከአንድነት እና ግለኝነት የትኛው ለሀገር ቀጣይነት ይበጃል የሚለውን በደንብ መረዳት አለበት›› ብለዋል፡፡ ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔር ፖለቲካ የተጠመደውን ማኅበረሰብ በማንቃት ረገድ እየሠሩ ቢሆንም ክፍተት እንዳለባቸውም አንስተዋል፡፡ ሀገራዊ አንድነትን ከሚሰብኩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመጣመር ለሀገሪቱ መጻኢ ዕድል መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ መልካሙ ሹምዬም የብሔር ፖለቲካው ረዥም ጊዜ ማስቆጠሩን ይጋራሉ፡፡ ‹‹የብሔር ፖለቲካው ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት ሲቀነቀን የዘለቀ በአለፉት 27 ዓመታት ደግሞ ጎልቶ የወጣ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን እየተመራችበት ያለው ሕገ-መንግሥት መሠረት ያደረገው ዜጋን ሳይሆን ብሔርን ነው፡፡ የዜግነት ፖለቲካ በተንጠልጠል ያለ እንጂ ሕገ-መንግሥቱ የሚያቀነቅነው ብሔርን ነው፡፡ የዜግነት ፖለቲካን በሀገሪቱ ላይ ለማስረጽ ሕገ-መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ መደረግ መቻል አለበት›› ብለዋል፡፡

‹‹የብሔር ፖለቲካ አያዋጣም›› የሚለውን የዶክተር ባንተይገኝ ሐሳብ ግን አቶ መልካሙ አይጋሩትም፡፡ የራሳቸውን ፓርቲ እንደምሳሌነት ወስደው ማንነትን መሠረት ያደረገ ሥሙ በአንድ ብሔር ቢጠራም አብረው የሚኖሩ ብሔሮችን ያቀፈ መሆኑን በመጥቀስ አካታች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ብሔር›› ከሚለው ቃል ይልቅ ‹‹ማንነት›› የሚለው የተሻለ እንደሚሆንም ሐሳብ አንስተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ የበለጠ ብዝኃነት ያላቸው የዓለም ሀገራት ሕገ-መንግሥታቸውን ሲያረቅቁ ዜጋን ወይንም ሕዝብን መሠረት ያደረገ እና በሀገሪቱ የሚኖሩ ሰዎችን እኩል ተጠቃሚ ያደረገ አድርገው ነው፡፡ በኢትዮጵያም የዜግነት ፖለቲካ እንዲኖር ከተፈለገ ሕገ-መንግሥቱ ዜጋን መሠረት ያደረገ ሆኖ መረቀቅ ይኖርበታል ሲሉም ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹የዜግነት ፖለቲካ በምኞት አይመጣም›› ያሉት አቶ መልካሙ ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው ኢሕአዴግ የብሔር ፖለቲካ የሚያራምዱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ኢሕአዴግን ሲታገሉና የዜግነት ፖለቲካን ሲያራምዱ ለረጅም ዓመታት የኖሩት ጠንካራ ፓርቲ መገንባት አልቻሉም፡፡ ይህ ደግሞ የብሔር ፖለቲካው ጠንካራ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፤ በአንጻሩ ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደካሞች ናቸው›› በማለት ሐሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡ አቶ መልካሙ በዜግነት ፖለቲካ ስም የብሔር ፖለቲካ የሚያራምዱ እንዳሉም አንስተው ሀገራዊ ፖለቲካ ለመመሥረት ከእንዲህ ዓይነት ትርክት ውስጥ መውጣት እንዳባውም አሳበዋል፡፡

አቶ መልካሙ ‹‹አሁን እየተመሠረቱ ያሉ የብሔር የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተመሠረቱለት ብሔር ውጭ ያለውን በጠላትነት የሚፈርጁ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በሕዝብ መካከል መቃቃር እየፈጠረ ነው፡፡ ፖለቲከኞች አካሄዳቸውን መቀየር አለባቸውም›› ብለዋል፡፡ ‹‹አብን ስሙ ብሔርን መሠረት አድርጎ የተነሳ ይሁን እንጂ ከአማራው ጋር የሚኖሩ ሌሎች ብሔሮችን በእኩል ለመጥቀም የሚሠራ፣ የትኛውንም ብሔር በጠላትነት የማይፈርጅ፣ እንደሌሎች የብሔር ፖለቲካ ፓርቲዎች መገንጠልን ሳይሆን አንዲት ኢትዮጵያን የሚያስብ እና የዜጎችን መብት የሚያስከብር ሀገራዊ ፓርቲ ነው›› ብለዋል፡፡

የብሔር የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመበራከት ይልቅ ጠንካራ የዜግነት ፓርቲ እንዲመሠረት ሕገ-መንግሥቱ መሻሻል አለበት የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸውም አስታውቀዋል፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ከተሻሻለ እና ሕዝብን ማመካከር ከተቻለ ወደዜግነት ፖለቲካ መሸጋገር እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡ ዋናውና ለሀገር ጠቃሚው ግን አንዲት ኢትዮጵያን ለመመሥረት በኢትዮጵያውያን የተዘራውን የውሸት ታሪክ እውነታውን በማውጣት በሕዝቦቹ መካከል እየመጣ ያለውን የመለያየት መንፈስ እና የመበዳደል መንፈስ ማስወገድ እንደሆነ ነው ያረዱት፡፡ ‹‹እውነቱን ሳያወጡ ‹በይቅርታ ይታለፍ› መባባል የልብ ፍቅር አያመጣም›› ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰበዓዊ መብት እና ፌደራሊዝም ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰሩ ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ ደግሞ ‹‹በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ውስጥ ሀገራዊ አንድነት አለ፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደስልጣን የመጡበትን ወቅት እና ስለሀገር አንድነት በተናገሩበት ጊዜ የነበራቸውን ደጋፊ ማስታወስ በቂ ነው›› ብለዋል፡፡ ዶክተር ሲሳይ ‹‹የዜግነት ፖለቲካ ተዳከመ እንጂ አልጠፋም፤ አይጠፋምም፡፡ በዜግነት ፖለቲካ ላይ ከተሠራ አሸናፊው የዜግነት ፖለቲካ ይሆናል›› ብለዋል፡፡ የዜግት ፖለቲካ ላይ የሚሠሩ አካላት ከመመሥረት ባለፈ ለሕዝቡ ዘለቄታዊ መፍትሔ የሚያመጡ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጥ የሚችል አቅጣጫ የሚከተሉ መሆን እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡

‹‹አብዛኞቹ የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች አደረጃጀታቸው በጓደኝነት እና ርዕዮተ ዓለምን መሠረት ያደረጉ በመሆናቸው የዜግነት ፖለቲካውን ደካማ እንዲሆን አድርጎታል›› ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰሩ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብዛታቸው ችግር ላይኖረው ቢችልም የሚነሱበት ጉዳይ ግን ብሔርን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ዘላቂነታቸው ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባም አብራርተዋል፡፡ የብሔር ፖለቲካ በሕገ-መንግሥቱ ያለ እና ሕገ-መንግሥቱን መሠረት ያደረገ ቢሆንም ሀገራዊ አንድነትን ለማምጣት እና ሀገር ለመገንባት ያለው አቅም ዝቅተኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

‹‹በቀጣይ የሚደረገውን ምርጫ ጨምሮ ለጥቂት ዓመታት የብሔር ፖለቲካ ሊያይል ይችላል፤ እኛ ኢትዮጵያዊ ነን ብለን እንዳናፍር የሚያደርግ የሰለጠነ ፖለቲካ፣ በማኅበረሰቡ የሰረፀ ዲሞክራሲ፣ እኩል ተጠቃሚ እና ተሳታፊ የሚያደርግ ሥርዓት መዘርጋት እና እያንዳንዱ አካባቢ በራሱ የሚተዳደርበትን መንገድ መፍቀድ ከተቻለ ኢትዮጵያዊ አንድነት የማይመጣበት ምክንያት የለም፡፡ ነገር ግን እኛ ሕገ-መንግሥት እንጂ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የለንም›› ሲሉም ስጋታቸውን ዶክተር ሲሳይ አካፍለዋል፡፡

የብሔር ፖለቲካ ዘላቂ አለመሆኑንና ችግር የወለደው መሆኑን በማመላከት ማኅበረሰቡ እየሰለጠነ ሲሄድ እና በሰፊው ማሰብ ሲችል ሥራቸውን እንደሚከስሙም ጠቁመዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ‹የምመርጠው ፓርቲ ምን የተሻለ ሊሠራልኝ ይችላል?› ከሚለው ሐሳብ ይልቅ ‹የማን ዘር ነው?› ወደሚለው ስለተሸጋገረ ቆም ብሎ በሰከነ መንገድ ጠቃሚውን መለየት እንደሚገባው ዶክተር ሲሳይ አሳስበዋል፡፡

በሀገራችን የብሔር ፖለቲካ መስፋፋቱን የጠቆሙት ዶክተር ሲሳይ ባለፉት ዓመታት ሌሎች ብሔሮች በብሔር ሲደራጁ የዜግነት ፖለቲካን እና ሀገራዊ አንድነትን በሰለጠነ መንገድ ሲያካሂድ የነበረው አማራ ችግሩ ሲበዛበት ወደተጠናከረ የብሔር ፖለቲካ እንደገባም አንስተዋል፡፡ ‹‹የሰው ልጅ በባሕሪው ዘላቂ ነገር ስለሚፈልግ የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች ዘላቂ መፍትሔዎችን በመቅረጽ ታላቅ ሥራ መሥራት መቻል አለባቸው፡፡ ሚዲያውንም በደንብ መጠቀም አለባቸው፤ በሀገሪቱ የሚታየው ብሔርተኝነት የጊዜ ጉዳይ እንጂ ወደዜግነት መምጣቱም አይቀርም›› ሲሉም መክረዋል፡፡

(አብመድ)


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE