የሱዳን ጉዳይ እና የአገራችን ነገር ( መንግስቱ ዲ.አሰፋ)

የሱዳን ጉዳይ እና የአገራችን ነገር ( መንግስቱ ዲ.አሰፋ)

Image result for sudan

የዛሬ 30 ዓመት በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጡት አዛውንቱ የሱዳን ርዕሰ ብሔር ዛሬ በሕዝብ ግፊት እና በመከላከያ ጣልቃ ገብነት ከሥልጣናቸው ወርደው የቤት ውስጥ እሥረኛ ሆነዋል።

አንዳንድ ጉዳዮች

የሱዳን ፖለቲካ መቀየር ወዴት እንደሚሄድ መገመት ይከብዳል። ለሁለት ዓመት የሚቆይ ወታደራዊ የሽግግር ሸንጎ በመቋቋሙ አገሪቷ ወደ ዴሞክራሲ የምታደርገው ጉዞ ለግምት አዳጋች ስለሚያደርገው። እስከዚያው ግን ለአገራችን ወሳኝ የሆኑ ገዳዮች ላይ ግንዛቤ እና ጥንቃቄ ያሻል።

1. ሊመጣ የሚችለውን ቀውስ ተከትሎ እና አገራችን በቅርቡ ባረቀቀችው የስደተኞች አዋጅ ተጠቅመው ብዙ የስደተኛ ጫና ሊደርስብን ይችላል። ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርም እንደዚያ።
2. የአልበሽር መንግሥት እጅግ ጠንካራ የሚባል ነበር። ያም ሆኖ ግን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ወደ አገራችን ሲደረገ የነበረው በሱዳን በኩል ነበር። አሁን ደግሞ ያለውን አመቺ ሁኔታ በመጠቀም በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ይችላል። ጥንቃቄ ያሻል።

Image result for sudan

3. የሚመጣው መንግሥትም ሕዳሴ ግድባችንን በተመለከተ የሚይዘውን አቋም አናውቅም። ግድቡ ከሱዳን ድንበር 40 ኪሎሜትር ብቻ ነው የሚርቀው። መንግሥታቸው ወታደራዊ ነው።
ሌላው ቢቀር የችግሩ መንሥዔ ኢኮኖሚ መውደቅ በመሆኑ ሚመጣው መንግሥት ጠንካራ ናሽናሊስት የመሆኑ እድል ከፍተኛ ስለሆነ አዲስ የድርድር ቅድመሁኔታ ሊጠይቅ ይችላል። ከግብጽ ጋር የመወዳጀታቸው እድል ከፍተኛ ነው።

4. የዐረቡ ዓለም መንትያ ፖለቲካ (ሳዑዲ-ግብጽ-የዐረብ ኤሚሬቶች) እና (ኳታር-ኢራን-ቱርክ) ጎራ ጉዳይ። አልበሽር ለሁለተኛው ቡድን ያደላ ነበር። ይህ አሜሪካን አያስደስታትም። ኢሥራዔልንም አይመስጣትም። የኢሳይያስ አፈወርቂ የማይጨበጥ አቋም አለ። ሶማሊያን አለመዘንጋት ነው።

ስለዚህ የአሜሪካ እንዱሁም ግብጽን ያካተተው የሳዑዲ ዐረቢያ ቡድን ፍላጎት በአፍሪቃ ቀንድ የመንሠራራት ምቹ እድል አለው ማለት ነው። እዚህ ጋር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ጥንቁቅ መሪ እና ጎበር ዲፕሎማት ያስፈልጋል።

አንድ እዚህ ጋር ጣል ማድረግ የምፈልገው ጥሩ አጋጣሚ አለ። የኢትዮጵያ አንድነት ሲባል ከሽራሮ እስከሞያሌ ነው። የትግራይ ፖለቲካ አሁን ጥግ መያዙ ትክክል አይደለም። እንደገና ድርድር ያስፈልጋል። አብሮነት ነው የሚያዋጣን። ህወሓትም አቋሙን መቀየር ያለበት ጊዜው የመጣ ይመስላል። በሱዳን የተፈጠረው ሁኔታ በግልጽ የሚያሳስበው ሁኔታ ይህንን ይመስለኛል። ጓዳቸው (የህወሓት) ሄዷላ! በመርህ እና በሕዝቦች ዘላቂ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ወዳጅነት ከአገር ውጪ አይገኝም። ቢገኝም አያዋጣም። አሁን ከአብይ እና ከአምባቸው ፓርቲ ጋር መነጋገሪያው ጊዜ ደርሷል። ይህንን ለነገ ሳይባል መጀመር አለባቸው። የትግራይ ልኂቃንም ነገን ዐይተው ለድርድሩ ህወሓት ላይ ግፊት ያደርጋሉ የሚል ቀና ግምት አለኝ። እኛ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ጠላት ወይም ወዳጅ እንደሌለ አውቀን ለዚህ መዘጋጀት አለብን። ያለፈው ጊዜ አልፏል። አንድነታችን እጅጉን የሚፈተንበት የውስጥ እና የውጭ ጫና ከምንም ጊዜ በላይ መጥቷል። መነቋቆሩን ትተን ለጋራ እንሥራ። የኢትዮጵያ ችግር በውጭ አልመጣምና መፍትሔውም ከውጪ አይመጣም። ሁሉ በእጃችን ነው።

ለሱዳን መልካሙን እመኛለሁ። የአብይ አህመድ አስተዳደርም ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ የአገራቸውን ጥቅም ያስከብራሉ፣ ለቀጠናውም ዘላቂ መረጋጋት እና ኢኮኖሚያዊ ትሥሥር ጠንክረው ይሠራሉ የሚል ተስፋ እናድርግ፣ ግፊትም እናድርድ!

 


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE