በተደራጀ አግባብ የተንቀሳቀሰ አካል አጥንቶ ሕዝብ ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ – አቶ ንጉሱ ጥላሁን

‹‹የኦሮሞንና የአማራን ሕዝብ በማጋጨት የከፋ ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግ ታቅዶ የተፈፀመ ይመስላል፡፡››

‹‹በተደራጀ አግባብ የተንቀሳቀሰ አካል አጥንቶ ሕዝብ ላይ ጉዳት አድርሷል››፡፡አቶ ንጉሱ ጥላሁን

በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ከሰሞኑ የተነሳው ግጭት ወደ ስፍራው በገባው የፀጥታ ኃይል እና በአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍ ቢረጋጋም ለጉዳዩ ዘላቂ እልባት እስካልተሰጠው ድረስ ከስጋት ነፃ መሆን እንደማይችሉ ነው ያነጋገርናቸው የከሚሴ ነዋሪዎች የተናገሩት፡፡

ከሚሴ ለዘመናት ሙስሊም ከክርስቲያን፣ ኦሮሞ ከአማራና ከአርጎባ፣ ቄስ ከቃልቻ ተከባብረው እና ተቻችለው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን የከተማዋ ነዋሪዎች አስታውሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህንን ውብ አብሮ የመኖር እሴትና አንድነት የሚፈታተኑ አደጋዎች ገጥመዋታል ብለዋል፡፡

የተፈጠረው ችግር የሕዝብ ግጭት አለመሆኑን የሚስማሙት አስተያየት ሰጭዎቹ፤ ለችግሩ ምክንያት ናቸው የሚሏቸው አካላት ከወረዳ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ የመንግሥት አመራሮች እና የተለየ ድብቅ ዓላማ ያላቸው ቡድኖች እንደሆኑ ይስማማሉ፡፡

‹‹የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ሊፈርስ ነው፤ ለዘመናት ዕውቅና ያገኘው ማንነታችሁም አደጋ ውስጥ ሊገባ ነው›› የሚል አሉባልታ በሰፊው መናፈሱ ለግጭቱ መንስኤ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪ መልአከ ገነት ደጀን ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አመራሩም የአሉባልታ ሰለባ ሆኗል›› ነው ያሉት፡፡

ወጣት ተሾመ ጥላዬ ደግሞ ‹‹ለተፈጠረው ግጭት አመራሩ ምክንያት እና ተሳታፊ በመሆኑ የክልሉ እና የፌደራል መንግሥታት በአግባቡ ሊመረምሩት ይገባል›› ብሎናል፡፡

የከሚሴ ከተማ ነዋሪው ሀጅ ሰኢድ ሙሐመድ እንዳሉት ደግሞ የተፈጠረው ግጭት የፖለቲካ ኪሳራ የደረሰባቸው ኃይሎች ሆን ብለው ያደራጁት እና የለኮሱት እሳት ነው፡፡ ‹‹ግጭቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ የሰው ሕይወትና ንብረት ሳያጠፋ በቁጥጥር ስር ማዋል የተቻለውም ሕዝብ አምኖና ተቀብሎ የፈጠረው ችግር ባለመሆኑ ነው›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ሕዝብ የየትኛውም የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች መጠቀሚያ አይደለም›› ያሉት ሃጂ ሰኢድ መንግሥት የችግሩን ጠንሳሾች በመለየት ለሕግ እንዲያቀርብም ጠይቀዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ‹‹እስካሁንም ድረስ የተፈጠሩት ሁሉም ግጭቶች የሕዝብ ግጭቶች አይደሉም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ሰሞኑን በከሚሴ፣ አጣዬ፣ ማጀቴ እና ካራ ቆሬ የተፈጠሩት ግጭቶችም የሕዝብ ግጭቶች አይደሉም›› ብለዋል፡፡

ችግሩ ከተፈጠረባቸው አካባቢዎች ሕዝብ፣ ከፀጥታ ኃይሉና ከግጭቶቹ አፈጣጠር ሂደት በመነሳት ባገኘነው መረጃ መሠረት ‹‹በተደራጀ አግባብ የተንቀሳቀሰ አካል አጥንቶ ሕዝብ ላይ ጉዳት አድርሷል››፡፡ ይህም የኦሮሞንና የአማራን ሕዝብ በማጋጨት የከፋ ሁኔታ እንዲኖር ለማድረግ ታቅዶ የተፈፀመ ይመስላል ነው ያሉት አቶ ንጉሱ ጥላሁን፡፡

ግጭቶቹ እንደተከሰቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የፀጥታ ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ አድርጎ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡ የመጀመሪያው ውሳኔም ግጭት የተፈጠረባቸውን አካባቢዎች ፀጥታ ለማረጋገጥ፣ ሰላምን ለማስፈንና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ሲባል ችግር ፈጣሪዎችን ለይቶ ሕጋዊ እና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ነበር ብለዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ልዩ ኃይል፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና የክልሉ ፖሊስ በጥምረት ባደረጉት ሰላም የማስከበር ጥረት ባለፉት ሦስት ቀናት የአካባቢው ሰላም ተሻሽሏል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ተፈቷል ማለት የሚቻለው የፀጥታ ኃይሉ አስተማማኝ ሰላም መኖሩን ማረጋገጥ ሲችል እና አጥፊዎች ተለይተው ለሕግ ሲቀርቡ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የፀጥታ ኃይሉ ከሕዝቡ ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን አቶ ንጉሱ ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡም ለጋራ ሰላሙ እና አንድነቱ ሲል አጥፊዎችን አጋልጦ መስጠት እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

(አብመድ)