ኦሮሞውን ከሶማሌው፣ ከጌዴኦው፣ ከጉሙዙ፣ ከሃረሬው …አሁን ደግሞ ከአማራው እያጣሉት ነው #ግርማካሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።

የኦሮሞ ጽንፈኞች፣ ኦነጎች፣ የጃዋር ቄሮዎችና በኦዴፓ/ኦህዴድ ውስጥ ያሉ ያልተደመሩ፣ ለነ ዶ/ር አብይና አቶ ለማ ራስ ምታት የሆኑ ዘረኛ አመራሮችና አባላት፣  በኦሮሚያ ክልልና በአማራ ክልል ከሚሴ ዞን ውስጥ በሚኖሩ፣ ኦሮሞ ባልሆኑ ማህበረሰባት ላይ፣ እንደዚሁም እነዚህን አካባቢዎች በሚያዋስኑ የሌሎች ክልሎችና ዞኖች ወረዳዎች በሚኖሩ ዜጎች ላይ የሽብር ተግባራት እየፈጸሙ እንደሆነ በገሃድ እያየን ነው።

በተለይም ዶ/ር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስተር ከሆኑና ኦህዴድ/ኦዴፓ በፌዴራል መንግስቱ የበላይነቱን ከያዘ በኋላ ፣ ጽንፈኞቹ በሕወሃት ጊዜ የማይታሰብ ድርጊቶችን ነው እየፈጸሙ ነው ያሉት። አንዳድን ዜጎች ህወሃት ይሻል ነበር እስከማለትም እየደረሱ ነው። በጌዴኦ ዶ/ር አብይ ተፈናቃዮችን ለማነጋገር ሄደው በነበረ ጊዜ ፣ አንድ የጌዴኦ እናት እንደተናገሩት፣ ምን አልባትም እነዚህ ሰዎች  “የኛ ሰው ስልጣን ይዟል፣ ማንም አይነካንም”  ከሚል አስተሳሰብ ይሆናል እኩል ዘር ተኮር ተግባራት ላይ የተጠመዱት።

ለምሳሌ የሚከተሉትን በግልጽ የሚታወቁትን መጥቀስ እንችላለን። ከእነዚህ ጽንፈኞች የተነሳ

 1. በኦሮሞ ክልል የቦረናና ጉጂ ዞኖችን በሚያዋስኑ አካባቢዎች የሚኖሩ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ሶማሌዎች በግፍ ተፈናቅለዋል፤፡ ብዙዎች ተገድለዋል።
 2. በጉጂ ዞን ውስጥ የሚኖሩ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ የጌዴዎና የቡርጂና ወገኖች በግፍ ተፈናቅለዋል።የሞቱም አሉ።
 3. ምእራብ ወለጋን በሚያዋስኑ የቤኔሻንጉል ክልል ወረዳዎች በሚኖሩ ጉሞዞች ላይ ኦነጎች በከፈቱት ጥቃት ምክንያት በተነሳው ግጭት፣ ከመቶ ሺህ በላይ ዜጎች ፣ አብዛኞቹ ኦሮሞዎች፣ ተፈናቅለዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል።
 4. በሃረር ዙሪያ ያሉ ጽንፈኛ ቄሮዎች የሃረርን ከተማ የዉህ መስመሮች ለወራት ዘግተው በከተማዋ ላይ ትልቅ ሽብር ፈጽመዋል።
 5. በአዲስ አበባ ዙሪያ በቡራዩ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ፣ በተለይም የጋሞ ማህበረሰብ ወገኖች ላይ አሰቃቂ ግፍና በደል ተፈጽሟል፡ ብዙዎች በጭካኔ ተገድለዋል። በአስር ሺሆች ተፈናቅለዋል፡
 6. በአዲስ አበባ ዙሪያ በለገጣፎ በሺሆች የሚቆጠሩ ዜጎች ጭካኔ በተሞላበት መልኩ መኖሪያ ቤታቸው እንዲፈርስ ተደርጎ ሜዳ ላይ ተጥለዋል።
 7. በአዲስ አበባ ዙሪያ በሱሉልታ፣ በለገጣፎ የተደረገውን ለመድገም፣ ኦሮሞ ያልሆኑትን ቤት ለይተው፣ ለማፍረስ ምልክት ተደረጎ ነዋሪዎች ለከፍተኛ ስጋት እንዲጋለጡ ተደርጓል።
 8. በኦሮሞ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞንን፣ ፈንታሌ ወረዳን በሚያዋስኑ፣ የምንጃርና የሸንኮራ አካባቢዎች የሚኖሩ የአማራና የአርጎባ ነዋሪዎች ላይ ጦርነት ከፍተው ብዙ ወገኖችን ተፈናቅለዋል፤ ብዙ ዜጎች ተገድለዋል። በዚሁ በፈንታሌ ወረዳ በምትገኘው የመተሃራ ከተማ፣ ኦሮሞ ያልሆኑ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ፣ በተለይም የአርጎባ ማህበረሰብት አባላት፣ ተፈናቅለው፣  በጊዜያዊነት በአፋር ክልል በምትገኝው የአዋሽ ከተማ ይገኛሉ።
 9. በአማራ ክልል የኦሮሞ ዞንን በሚያዋስኑ በአጣዬ፣ ማጄቴና ካራቆሬ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ላይ፣  በስፋት እየተዘገበ እንዳለው፣  ከፍተኛ የሽብር ተግባራት ተፈጽመዋል።፡ ዜጎች ተገድለዋል። ቤተ እምነቶች ተቃጥለዋል።
 10. አዲስ አበባ የኛ ናት በሚል በአዲስ አበባ ላይ የኦሮሞ የበላይነትና ልዩ ጥቅም እንዲጠበቅ በተቀናጀ መልኩ እንቅስቃሴ ተደረጓል። ሕጉን ተከትለው ለኮንዶሚኒየም ገንዘብ ያዋጡ ዜጎች፣ ቤታቸው ይገቡ ዘንድ ፣ መጀመሪያ እጣ እንዳይወጣ ለማድረግ ዘመቻ ተደረጓል። እጣ ከወጣ በኋላ ደግሞ እጣ የወጣላቸው ቤታቸው እንዳይገቡ ተከልክለዋል።
 11. በሃረርጌ አካባቢ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ሶማሌዎችን ተፈናቅለዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል። በአንድ ቀን በአወዳይ ከስድሳ በላይ ሶማሌዎች መታረዳቸው የሚታወስን ነው።በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎችም ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለዋል።

እንግዲህ ከላይ የተዘረዘሩትና ሌሎች ፣ ምን ያህል የኦሮሞነት ፖለቲካ አገርን እያተራመሰ ያለ ፖለቲካ መሆኑን ፍንትው አድርጎ በግልጽ የሚያሳይ ነው።

ይህ የኦሮሞ ጽንፈኝነት እንዲባባስ ምክንያቶች ናቸው ብዬ በዋናነት የማስቀምጣቸው  ሁለት ናቸው።

አንደኛው – ላለፉት ሃያ ስምንት አመታት የተዘረጋው የዘር ፖለቲካ፣ የዘር ሕገ መንግስትና የዘር አወቃቀር ነው። አሁን ያለው ሕገ መንግስት ኦሮሚያ የሚል ክልልና በአማራ ክልል ውስጥ ኦሮሞ የሚል ዞን ሸንሽኗል። የኦሮሞ ማሀበረሰብ ከሌላው ጋር የተሳሰረ፣ የተዛመደና የተዋለደ  ሆኖ፣ የተለየ የኦሮሞ ማህበረሰብ ለመፍጠር ተሞክሯል። ኦሮሞውን ከሌላው ለመለየት ብዙ ተሰርቷል። ኢትዮጵያን ያቀኑት በዋናነት የሚጠቀሱት ብዙዎቹ የኦሮሞ ጀግኖ አባቶች ሆነው፣ ኦሮሞ በኢትዮጵያ ላይ ምንም ድርሻ እንደሌለው አይነት ተደርጎ ነው ፣ የዉሸት ትርክቶች በመፍጠር ፣ የዉሸት ታሪክ በማስተማርና የጥላቻ ሃዉልቶችን በማቆም፣ የብዙ ኦሮሞ ልጆች አይምሮ እንዲበላሽ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ እንዲጠሉ፣ የኢትዮጵያን ፊደል እንዲሸሹ፣ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር እንዳይግባቡ የተደረገው። ትልቁ ምክንያትና ችግር ይሄ ነው።

ሁለተኛ –  ሳያስቡት ይህ የጽንፈኝነት  ችግር እንዲባባስ ካታሊስት የሆኑት ደግሞ በዋናነት የዶ/ር አብይ የፌዴራል የአቶ ለማ መገርሳ የኦሮሞ ክልል መስተዳደሮች ናቸው። “ለምን ?”  ብትሉ፣  እነርሱ ናቸውና  ኦነጎችንና  እነ ጃዋርን፣ ወጪዎቻቸውን ሸፍነውና ለምነው  አገር ቤት እንዲገቡ ያደረጓቸው። የነ ዶር አባይ አላማ ቀናና ጤናማ አላማ ነበር። “ማንም ማኩረፍ የለበትም፣ ልዩነቶች ቢኖሩንም በምርጫ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንፈታዋለን” በሚል ነበር ሆደ ሰፊ የሆኑት። ሆኖም ግን ተለምነው አገር ቤት የገቡት ጽንፈኛ ቡድኖች፣ ያከበሯቸውን የነአቶ ለማን ዉለታ መከፈል የጀመሩት፣ እነ አቶ ለማ መገርሳ አላማቸው እንዳይሳካላቸው ለማድረግ ሽብርን በመንዛት ነው።

ያለ ምንም ከልካይ፣  የፈለጉት እንዲያደርጉ ስለተፈቀደላቸው፣ እነ ጃዋርና ፕሮፌሰር ጫት (ሕዝቄል) በየቦታው እየዞሩ ጥላቻን ሰብከዋል። የሚቆጣጠሩት ሜዲያ ኦ.ኤም.ኤን በነጻነት እንዲንቀሳቀስ ተደርጓል። እነ በቀለ ገርባም በይፋ ፣”ኦሮሞ ካልሆነ አታግቡ፣ በኦሮማኛካልሆነ አትነገዱ …” አይነት ሂትለራዊ የጥላቻ ንግገ ሲናገሩ ሰምተናቸዋል። ኦነጎች “ትጥቅ ፈተዋል” ተብሎ ተነገረን። ግን ዉሸት ነበር። እነ ዳዎድ ኢብሳ ትጥቅ አንፈታም ብለው ፣ በወለጋ፣ በጉጂና በቦረና አካባቢዉን የጦርነትና የሽብር ቀጠና አደርገዉታል። ባንኮችን ሸርፈዋል።መሰረተ ልማቶችን አፍርሰዋል።  ላለፉት ቀናት ደግሞ በስፋት እንደተዘገበው በሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ አካባቢ ሽብር እየፈጠሩ ነው።

እንግዲህ አሁን ባለው አካሄድ ፣ በኔ እይታ፣  ያሉ ችግሮች የበለጠ እየተባባሱ እንጂ ነገሮች እየተስተካከሉ በመምጣት ላይ አይደሉም። የዶ/ር አብይ አስተዳደር የሳንባ ነቀርሳ በሽታን ቀላል ጉንፋን ይመስል የጉንፋን መድሃኒት እየሰጠ ማስቀጠል አይቻልም። ንግግሮች ማድረግ፣ የሕዝብ ለሕዝብ የሚባል መድረኮችን ማዘጋጀት፣ እናቶችን በየከተማ ስለ ሰላም እንዲናገሩ ማሰማራት፣ የሰላም ሚኒስቴር ብሎ ሰላም እንዲመጣ ብቻ መመኘና  የመሳሰሉ መፍትሄዎችን ብቻ ማስቀመጥ በሳንባ ነቀርሳ ለተጎዳ በሽተኛ የጉንፋን መድሃኒት እንደ ማዘዝ ነው።

ለአገራችን ብችኛው መፍትሄ፣ በኔ እይታ፣  አሁን ያለውን የጎሳ አወቃቀርን ሙሉ ለሙሉ አፍርሶ፣  በዜግነት ላይ ያተኮረ፣ ሁሉንም እኩል የሚያይ መንግስታዊ አወቃቀርን መዘርጋትና ሕግ መንግስቱን በብሄር ብሄረሰብ ህዝብ በሚሉት በዘዉግና ዘር ላይ ሳይሆን በዜጎች መብት ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረግ ነው።

ይህ ካልሆነ ወደ ባሰና የከፋ ደረጃ ነው የምንወድቀው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚጎዳው፣  ከሁሉም ጋር በነዚህ የኦሮሞ ጽንፈኞች እንዲጠላ እየተደረገ ያለው የኦሮሞ ማህበረሰብ ነው። እስቲ አስቡት፣ በሶማሌዎች ላይ ጽንፈኛ ኦሮሞዎች ጥቃት ሲፈጸሙ ሶማሌዎች የአጸፋ መልስ በመመለሳቸው ከስድስት መቶ ሺህ በላይ ኦሮሞዎች ተፈናቅለዋል። በቤኔሻንጉል ኦነጎች የጉሙዝ ሃላፊዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘራቸው፣ ጉሙዞች በወሰዱት የአጸፋ ምላሽ ከመቶ አምሳ ሺህ በላይ ብዙዎቹ ኦሮሞዎች  ከቤኒሻንጉል ክልል ተፈናቅለዋል። አሁን እንደገና ከአማራው ማህበረሰብ ጋር በምስራቅ ሸዋና በሰሜን ሸዋ ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ፣ በአሰላ..አሁን እያየነው ያለ ነገር እየተቀጣጠለ ከመጣ ትልቅ እልቂት ነው የሚከሰተው። የኦሮሞ ማህበረሰብ የሚጠቀመው ሰለም፣ ፍቅርና አንድነት ሲኖር ብቻ ነው። ከሶማሌዎች ፣ ከጌዴዎች፣ ከሃረሬዎች፣ ከአማራዎች፣ ከአርጎባዎች ፣ ከጉሙዞች…ከስንቱ ጋር ተላትመው ሊዘለቁ ነው ??????ይታሰብበት እላለሁ !!!!!