ዓለማቀፉ የጸረ-ሥቅየት ድርጅትና አባል ተቋማት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በሦስት ሲቪል ማኅበራት ላይ የጣለውን እገዳ “ያለምንም ቅድመ ኹኔታ” እንዲያነሳ ጠይቀዋል።
ድርጅቶቹ ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ መንግሥት በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይ የሚያደርገውን “ማስፈራራት” እና “ዛቻ” እንዲያቆም፣ ለሲቪል ማኅበራትና ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ምቹ ኹኔታ እንዲፈጥርና የመደራጀትና ሃሳብን የመግለጽ መብቶችን እንዲያከብር ጥሪ አድርገዋል።
ድርጅቶቹ፣ መንግሥት በታገዱት ማኅበራት ላይ ያቀረበው ክስ “መሠረተ ቢስ” እና “ፖለቲካዊ ዓላማ ያዘብ ነው” በማለት ተችተዋል። የኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር ዳን ይርጋ እና የሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት መሪዎች በደረሰባቸው “ማስፈራሪያ” እና “ዛቻ” ከአገር መሰደዳቸውንም ድርጅቶቹ ጠቅሰዋል።