ከ60 ሔክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ የለማ ሸንኮራ አገዳ ሙሉ ለሙሉ በእሳት ወደመ

በኦሮሚያ ክልል ፣ሆሮጉድሩ ወለጋ ዞን ፣ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ንብረት የሆነና ከ60 ሔክታር በላይ በሚሆን መሬት ላይ የለማ ሸንኮራ አገዳ ሙሉ ለሙሉ በእሳት መውደሙን ከፋብሪካው ሠራተኞች ተሰምቷል

ሸንኮራ አገዳው በሦስት የተለያዩ ቦታዎች ላይ የለማ መሆኑን የጠቀሱት ሰራተኞቹ፣ አደጋው የተከሰተው ትላንት ኅዳር 19/2017 ዓ.ም ከቀኑ 6፡30 አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሸንኮራ አገዳው በተጨማሪ ንብረትነቱ የስኳር ፋብሪካው የሆነ ዋጋው እስከ 40 ሚሊዮን ብር የሚገመት ማሽን በእሳቱ ተቃጥሎ ከጥቅም ውጪ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል።

ሰራተኞቹ እሳቱን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ከስድስት ሰዓታት በላይ እንደፈጀና ምሽት 1 ሰዓት አካባቢ ማጥፋት መቻላቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በሸንኮራ ልማቱ ላይ በተደጋጋሚ የእሳት ጥቃት ፈፅመው ያውቃሉ። የአሁኑ አደጋ መንስኤ እስካሁን በይፋ አልታወቀም።