ብልሹው የግብይት ሥርዓት ውስጥ ያለው ውጥንቅጥ የሚስተካከለው በሰዶ ማሳደድ ዘመቻ ሳይሆን፣ በሙያዊ ክህሎት በዳበረ ጥናት ላይ የተመሠረተ አሠራር ብቻ ነው፡፡ ይህንን ጥንቅቅ ያለ አሠራር ለማግኘት ደግሞ የግብይት ሥርዓቱን በስፋትና በጥልቀት የሚያውቁ ባለሙያዎች ዕገዛ ያስፈልጋል፡፡ በመርካቶ ገበያም ሆነ በሌሎች መገበያያዎች ቀደም ሲል ጀምሮ የሚታወቀው የግብይት ዘይቤ፣ ውስጡ ሲመረመር በርካታ ውጫዊ እጆች ጭምር የሚተራመሱበትና በእጅጉ የተጠላለፈ ነው፡፡ ከአገር ውስጥ አምራቾችም ሆነ ከውጭ አስመጪዎች የሚገኙ የተለያዩ ምርቶችና ሸቀጦች፣ ከጅምላ አከፋፋዮች እስከ ቸርቻሪዎች የሚያልፉባቸው ቅብብሎሾች ከደጅ እንደሚታየው በቀላሉ የሚከናወኑ አይደሉም፡፡ ለእያንዳንዱ የምርት ዓይነት የሚቆረጥ ደረሰኝ የምርቱን መጠንና ዋጋም አመላካች አይደለም፡፡ ጅምላ ሻጩ ከአምራቹ ወይም ከአስመጪው ሲረከብ ደረሰኝ ላይኖረው ይችላል፡፡ ቸርቻሪው ዘንድ ደግሞ ጭራሹን አይታሰብም፡፡ የደረሰኝ ዘመቻው በጥናት ካልተመራ ውጤቱ ትርምስ ነው፡፡
መርካቶ ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ የሚደረግበትና ለመላ አገሪቱ ጭምር የበርካታ ምርቶች መገኛ ማዕከል ብቻ ሳይሆን፣ የሁሉም ዓይነት ምርቶች ዋጋ የሚወሰንበት ወሳኝ ሥፍራ ነው፡፡ ከፍጆታ ዕቃዎች ጀምሮ ሁሉም ዓይነት ምርቶች ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚሠራጩበት ይህ ታላቅ ገበያ፣ ለረጅም ጊዜ ንግዱን የተቆጣጠሩ ውስን ግለሰቦች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅዕኖአቸውን ያሳርፉበታል፡፡ እነሱ ለሁሉም ምርቶች ሊባል በሚችል ሁኔታ ዋጋ ወሳኝ ከመሆን አልፈው፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን በመቆጣጠር እንዳሻቸው የማድረግ ኃይልም እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ከእነሱ በስተጀርባ ደግሞ የተሰጣቸውን መንግሥታዊ ሥልጣን ላልተገባ ጥቅም የሚገለገሉበት ትከሻቸው የደነደነ ሹማምንት እንዳሉም መረሳት የለበትም፡፡ መንግሥት የመርካቶ ገበያን ተግዳሮቶች ፈር አስይዞ ጠቀም ያለ ግብር መሰብሰብ ከፈለገ፣ ከለብለብ ዘመቻ ወጥቶ በጥናት ላይ የተመሠረተ አሠራር ይዘርጋ፡፡ በዘፈቀደ የሚደረግ ዕርምጃ ሌቦችን ከመፈልፈል የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡
በአጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱን መላ ቅጥ ካሳጡት ችግሮች መካከል አንዱ የመንግሥት የቁጥጥር ሥርዓት አለመዘመን ነው፡፡ ይህም የሚገለጽባቸው በርካታ ማሳያዎች ቢኖሩም ዋና ዋናዎቹ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ከዋጋ በታች እንደተገዙ (Under Invoicing) ተደርገው አገር ውስጥ መግባታቸው፣ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ካሉ ቀላል ቁጥር የሌላቸው በታክስ መረቡ ውስጥ አለመኖራቸውና ቢኖሩም ግብር ሰዋሪዎችና አጭበርባሪዎች መብዛታቸው፣ የውጭ ምንዛሪ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ውጭ የሚያሸሹ መኖራቸው፣ በሐሰተኛ ደረሰኝ በርካታ ግብይቶች መደረጋቸው፣ እንዲሁም የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት የሚያሰማሯቸው ተቆጣጣሪዎች የሕገወጦች ተባባሪ መሆናቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ ከተጠቀሱ ጥቂት ማሳያዎች በተጨማሪ በርካታ የረቀቁ ሕገወጥነቶች እንዳሉ የታወቀ ነው፡፡ ብልሹውን የግብይት ሥርዓት መልክ ማስያዝ የሚቻለው፣ ከነጋዴዎች በተጨማሪ መንግሥት የራሱንም ሰዎች መቆጣጠር የሚያስችለው አቅም ሲገነባ ብቻ ነው፡፡ ይህ ባልሆነበት ዘመቻው የሌቦች ሲሳይ ነው የሚሆነው፡፡
ጤነኛ የሚባል የግብይት ሥርዓት ዋነኛ ተዋናዮቹ ማለትም ሸማች፣ ነጋዴና መንግሥት እየተናበቡበት በሥርዓት ይካሄዳል፡፡ እነዚህ ሦስት አካላት በሚገባ ካልተናበቡ የግብይት ሥርዓቱ ይታወካል፡፡ በተለይ ኢኮኖሚው በነፃ የገበያ ሥርዓት ይመራበታል በሚባልበት አገር ውስጥ የግብይት ሥርዓቱ ከታወከ፣ በሥርዓተ አልበኞች ለመወረሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ ሦስቱ አካላት ካላቸው ሚናና ኃላፊነት አንፃር የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ በነፃ ገበያ ሥርዓት ውስጥ ነጋዴዎች ጤናማና ፍትሐዊ በሆነ ውድድር መፎካከር አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በስፋት የሚታየው አልጠግብ ባይ ነጋዴዎችና ደላሎች የመወዳደሪያ ሜዳውን መውረራቸው ነው፡፡ በአምራችነት፣ በአስመጪነት፣ በጅምላ አከፋፋይነትና በቸርቻሪነት ሥራዎች ውስጥ የተሰማሩ የተወሰኑ የተደራጁ ኃይሎች ጤናማ ውድድርን አጥፍተዋል፡፡ የምርትና የአቅርቦት ሰንሰለቶችን በመቆጣጠር ዋጋ እንደፈለጉ ይወስናሉ፡፡ የአቅርቦትና የሥርጭት መስመሮችን ይዘጋሉ፡፡ ሰው ሠራሽ እጥረት በመፍጠር ዋጋ ይቆልላሉ፡፡ ሰላማዊና ጤናማ መሆን የሚገባውን የውድድር ሜዳ በማጣበብ ሕገወጥነትን ያሰፍናሉ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የግብይት ሥርዓቱ በጤናማ ውድድር ስለማይመራ ከፍተኛ በደሎች ተፈጽመዋል፡፡ በነፃ ገበያ ሥርዓት ስም ገበያው መረን ተለቆ ሸማቾች ያለ መንግሥታዊ ጥበቃ ሲበዘበዙ ተመልካች የለም፡፡ የሁሉም ምርቶች አቅርቦት በጥቂት የንግዱ ተዋናዮችና ከለላ ሰጪ ባለሥልጣናት ታንቆ፣ ከነፃ ገበያ ሥርዓት በተቃራኒ ግብይት ሲከናወንና ጥቂቶች ከመጠን በላይ ሀብት ሲያጋብሱ የሚቆጣጠር የለም፡፡ ግብር ከማጭበርበርና ከመሰወር ታልፎ በይፋ የኮንትሮባንድ ንግድ ተስፋፍቶ ከአቅም በላይ ሲሆን፣ ከዚህ በስተጀርባ ያሉ ሥውር እጆች ያለ ከልካይ ያሻቸውን እያደረጉ አገር እየደማች ነው፡፡ ኤክስፖርት ተደርገው ለአገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ያለባቸው ምርቶች ታግተው፣ በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት አገሮች እየወጡ እየደረሰ ያለው ኪሳራ ከሚታሰበው በላይ እየሆነ ነው፡፡ ብልሹው የግብይት ሥርዓት ጥቂቶች በሕገወጥ መንገድ የተንደላቀቀ ሕይወት የሚመሩበት መሆኑ ከማስገረም አልፎ ያስቆጫል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ባለፈው ሳምንት ለከተማው ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፣ በተደረገ ጥናት ማወቅ የተቻለው የሁሉም የሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ትኩረት ፊት ለፊት የሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ ነው ብለዋል፡፡ የዕቃዎች ምንጭ ላይ ግን ትኩረት አለመደረጉን ገልጸው ከውጭ የሚገቡ ከሆነ የጉምሩክን መረጃ ይዞ መሥራት እንደሚያስፈልግ፣ አገር ውስጥ ከሚያመርቱ ፋብሪካዎች ከሆነ ደግሞ አከፋፋዮች ለምን ያለ ደረሰኝ ያከፋፍላሉ የሚለውን መመለስ የመንግሥት ግዴታ ነው ብለዋል፡፡ ከጥንት ጀምሮ የመንግሥት ኃላፊነቶች ከሆኑት መካከል አንዱ ግብር መሰብሰብ መሆኑን፣ ግብር ደግሞ ፍትሐዊነት ማስፈኛ መሆኑንና ሕጋዊ የግብይት ሥርዓት ማስተካከያ እንደሆነም አክለዋል፡፡ መርካቶ ውስጥ ከሚገመተው በላይ ችግር እንዳለ ጥናቱ እንደሚያሳይም ገልጸዋል፡፡ ግብር መክፈልም ሆነ ደረሰኝ መቁረጥ ግዴታ መሆኑን አስምረውበታል፡፡ መንግሥት እንደተባለው በዚህ ደረጃ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ውስጡን እያጠራ ከዘመቻና ከግርግር ይታቀብ፡፡ ዘመቻ ብልሹውን የግብይት ሥርዓት እንደማያፀዳውም ግንዛቤ ይኑር!