“አደጋው በጣም አሳዛኝና ልብ የሚሰብር ስሜት ነው የፈጠረብኝ” አደጋው በአውሮፕላን አብራሪዎች ላይ ምን ስሜት ፈጠረ?

BBC Amharic

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላን አደጋ 157 ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ የኢትዮጵያዊያንን፣ የኬንያዊያንን፣ የጣሊያናዊያንን እና ሌሎች የሠላሳ ሃገራትን ልብ ከመስበር አልፎ ዓለምን በጠቅላላ በድንጋጤ ያናወጠ ክስተት ነበረ።

ይህን አደጋ ተከትሎ ከሃምሳ በላይ ሃገራትም ሁኔታው ተጠንቶ፣ ተጣርቶና የመረጃው ሳጥን ውጤት ይፋ እስኪደረግ ቦይንግ 737 ማክስ ኤይት አውሮፕላኖቻቸውን ከመብረር ማገዳቸውም ይታወሳል።

በዚህም ወቅት የተለያዩ ሰዎች ሐዘናቸውን የገለፁ ሲሆን ባለፈው እሑድ ኢትዮጵያ ውስጥ ተምሳሌታዊ ቀብር ሥነ-ሥርዓት ሲደረግ በኬንያ ደግሞ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ በሙሉ የፀሎት ሥነ-ሥርዓት ተዘጋጅቶ ነበር።

ዜናው በርካቶች ላይ ጥልቅ ሐዘንን የፈጠረ ቢሆንም ለሥራው ቅርብ የሆኑት የአውሮፕላን አብራሪዎች ላይ ተለየ ስሜትን መፍጠሩ አይቀርም። እኛም ሁለት አብራሪዎችን ከአደጋው ጋር ተያይዞ የተፈጠረባቸውን ስሜት እንዲያጋሩን ጠይቀናቸው ነበር።

ካፕቴን መኮነን ብሩክ አውሮፕላን አብራሪ ከሆነ ከሦስት ዓመታት በላይ የተቆጠሩ ሲሆን፤ አርሱም ሴስናር ካራቫን 208 የተሰኙ አውሮፕላኖች ያበራል። ትውስታውን ወደዛች አሳዛኝ ዕለት መለስ ባደርገነው ጊዜ መኮነን ጥልቅ ሐዘኑን ገልፆ “በረራ 302 እንደወደቀ እኛ ወደ ጂንካ ለመብረር በመዘጋጀት ላይ ነበርን። በረራ 302 አስቸኳይ ጥሪ ማስተላለፉንና እንደሚመለስ ከበረራ መቆጣጠሪያ ማማው ሞተራችንን አጥፍተን እንድንጠብቅ በራድዮ ትዕዛዝ አስተላለፉልን” ይላል።

ካፕቴን መኮነን የሚያበረው ትንሽ አውሮፕላን ሲሆን፤ የ12 ሰዎችን ነፍስ በአየር ላይ ይዞ መጓዝና ከ170 በላይ ሰዎችን አሳፍሮ በመጓዝ መካከል ትልቅ ልዩነት ቢኖርም እንኳን ሁሉም የአየር ጉዞ እራሱን የቻለ ስጋትና ውጥረት እንዳለው ይናገራል።

“ከግማሽ ሰዓት በኋላ በራድዮ አውሮፕላኑ ከራዳር እንደወጣና በአየር ኃይል ፍለጋ እንደተጀመረ ሲነገረን መከስከሱ ወዲያውኑ ነበር የገባኝ” የሚለው ካፕቴን መኮነን አክሎ በናሽናል ጂዮግራፊ ‘ኤርክራሽ ኢንቬስትጌሽን’ ፕሮግራሞች እንደሚያስረዱት አውሮፕላን ከራዳር ጠፋ ማለት መጥፎ ነገር እንደተከሰተ የሚያሳይ የመጀመሪያው ምልክት ነው በማለት ያስረዳል።

“መከስከሱን ተረዳን፤ ወዲያውኑ በራድዮ የመብረር ፈቃድ ተሰጠንና ልባችን እንደተሰበረ ወደ ጂንካ አመራን” ይላል። ካፕቴን መኮነን ከሴስናር ካራቫን 208 አውሮፕላን አብራሪዎች ጋር

 ካፕቴን መኮነን ከሴስናር ካራቫን 208 አውሮፕላን አብራሪዎች ጋር

ሜሮን አመሃ በአሜሪካ አየር ኃይል ውስጥ በተንታኝነት የሠራች ሲሆን፤ በሥልጠና ወቅት ለአየር ኃይል አብራሪነት የበረራ ሥልጠና ወስዳ ሰርቲፊኬት ለመውሰድ 100 ሰዓታት የሚቀሯት ቢሆንም “የምይዘውን አውሮፕላን የማላውቀው ከሆነ ምንም ሰላም አይሰጠኝም” ትላለች።

“አደጋው በጣም አሳዛኝና ልብ የሚሰብር ስሜት ነው የፈጠረብኝ” የምትለን ሜሮን ብዙውን ጊዜ የአውሮፕላን አደጋ በሚሰማበት ወቅት በእውቀት እጥረት ወይም በቴክኒክ ብልሸት የተፈጠረ ነው ተብሎ እንደሚጠረጠርም ትናገራለች።

“እንደዚህ ዓይነት አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ የብዙዎችን አውሮፕላን አብራሪ ችሎታ፣ አቅምና እውቀታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው” የምትለን ሜሮን “ይህም ሙያችንን የሚያሰድብና የሚያስጠይቅ ክስተት” ሊሆን የሚችል ነበር ትላለች።

ነገር ግን የአሁኑ አደጋ “የአውሮፕላኑ ችግር በመሆኑ በይበልጥ ልብ የሚሰብር ነገር ነው። ለብዙዎች ሕይወት ኃላፊነት ይዞ ለሚያበር ሰው ብቻ ሳይሆን ለተሳፋሪ እራሱ ለማመን የሚከብድ እውነታ ነው። ምክንያቱም የአውሮፕላን ችግር በማንም ሊፈታ የሚችል አይደለም” ትላለች። አክላም ኃላፊነቱን የሚወስደው ማን እንደሆነም ሊታሰብበት ይገባል ስትል ትጨምራለች።

ካፕቴን መኮነን “እኛ የምንይዘው አውሮፕላን አነስ ያለ በመሆኑ በወቅቱ ምንም ብናዝንም የበረራ ጉዟችንን ለመቀጠል ብዙ አልከበደንም ነበር። በዚያን ሰዓት ትልቅ አውሮፕላን የምንይዝ ቢሆን ኖሮ በጣም እንደነግጥ ነበር። ግን ዞሮ ዞሮ እንጀራችን ስለሆነ ምንም ማድረግ አልቻልንም አበረርን” ይላል በሐዘን በተሰበረ ስሜት።

በቁጥር ሲታይ፤ ከመንገድ ትራንስፖርት ጋር የተያያዙ አደጋዎች ከአየር አደጋዎች አንፃር እጅግ በጣም ይበዛሉ። በዓለም ዙሪያ በዓመት ቢያንስ 1.2 ሚሊዮን ሰዎች በመንገድ ትራንስፖርት አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የዓለም አቀፍ የመንገድ ትራንስፖርት ደኅንነት ማኅበር ይገልፃል።

በአየር ትራንስፖረት የሚፈጠሩ አደጋዎችን በምንመለከትበት ጊዜ ደግሞ ከዓመት ዓመት የሚለያይ ሲሆን ለምሳሌ እ.አ.አ በ2016 በዓለም ዙሪያ 325 ሰዎች፣ በ2017 ከ37 ሚሊዮን በረራዎች 13 ሰዎች፣ በ2018 ደግሞ 500 ሰዎች በአውሮፕላን አደጋ ሳቢያ በሞት ተቀጥፈወል።

የአየር ትራንስፖርት አደጋዎች ከቁጥር አንጻር ዝቅተኛ ነው። “እኛ ሁሌም በአየር ላይ ነንና ሰው ሠራሽ ነገር ምንጊዜም ዘላቂነት የለውም። አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ ሁላችንንም ነው የሚነካን፤ ምክንያቱም እንደ ቤተሰብ ነን” የሚለው ካፕቴን መኮነን “ሰው የቤተሰቡን አካል ሲያጣ ምንም ማለት አይችልም ከማዘን ሌላ። ግን እኔ ማብረሬን አላቆምም” ይላል።

ሜሮን ደግሞ “እንደዚህ ዓይነት አደጋ በምሰማበት ወቅት ለማብረር ያለኝ ፍላጎትና ባለሙሉ ልብነት ላይ የራሱ የሆነ ውጤት ይኖረዋል” በማለት አደጋው ከፈጠረባት ሃዘን ባሻገር ያለውን ውጤት ገልፃ፤ ሁሉንም የሚነካ አደጋ እንደመሆኑ “የአደጋው መንስዔ ውጤቱ ቢታወቅ ለአብራሪዎችም ሆነ ለተጓዦች በሙሉ ልብ ለመብረር ተስፋ ይሰጣል፤ ለዚህም ነው በጉጉት ውጤቱን የምንጠባበቀው” ትላለች።