በነበረከት ስምዖን ቤተሰቦች ላይ የሚደርሰው ዛቻ እንዲቆም ትዕዛዝ ተላለፈ።

የባህር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ በአቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ ላይ የጠየቀውን የ8 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

ፍርድ ቤቱ በዛሬው እለት በጥረት ኮርፖሬት የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል የተጠረጠሩትን አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳን ጉዳይ ተመልክቷል።

የክልሉ ፀረ ሙስና ኮሚሽን የወንጀል መርማሪ ባለፉት 8 ቀናት በተሰጠው የምርመራ ጊዜ የተለያዩ ሰነዶችን መመልከትና የሰው ምስክሮችን ቃል ከሃገር ውስጥና ከውጭ ማሰባሰቡን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

ይሁን እንጅ የዳሽን ቢራ አክሲዮን ሽያጭን በተመለከተ የሚሰራውን ስራ የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አለማጠናቀቁንና ለዚህም ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በደብዳቤ አሳውቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው መርማሪ ባለፈው የችሎት ውሎ በተሰጠው ቀን ተጠቅሞ ስራውን ማጠናቀቅ ይገባዋል በማለት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁ አግባብ አይደለም በማለት ተቃውመዋል።

አያይዘውም ባለፈው ጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም በነበረው ቀጠሮ የኦዲት ስራው 90 በመቶ ተጠናቋል መባሉን ጠቅሰው አሁን ላይ አልተጠናቀቀም መባሉ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ አንጻርም ፍርድ ቤቱ በነጻ ሊያሰናብታቸው እንደሚገባም ጠቅሰዋል፤ እስካሁን በማረሚያ ቤት መቆየታቸው አግባብ አለመሆኑንም ነው ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት።

ከዚህ ባለፈም ተከላካይ ጠበቃ የማቆም መብታቸው እንዲከበርና በቤተሰቦቻቸው ላይ እየደረሰ ያለው ዛቻና ማስፈራሪያ እንዲቆምም ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

መርማሪ በበኩሉ የዳሽን ቢራ አክሲዮን ሽያጭ ብቻ 90 በመቶ አለመጠናቀቁን በመጥቀስ፥ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቁ ሌሎች ስራዎች መኖራቸውንና በነገው እለትም አቶ ታደሰ ካሳን ጨምሮ በ9 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንደሚመሰርት ገልጿል።

የኦዲት ስራውም ካለው ውስብስብ ባህሪ አንጻር ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው አስረድቷል።

የግራ ቀኙን ያደመጠው ፍርድ ቤቱም መርማሪ የጠየቀውን የ8 ተጨማሪ የምርመራ ቀን በመፍቀድ፥ የተጠርጣሪዎች ጠበቃ የማቆም መብት እንዲከበርና ቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰው ዛቻ እንዲቆም ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ትዕዛዝ አስተላልፏል።