ለሕዳሴው ግድብ የሕብረተሰቡ ድጋፍ ቀዝቅዞ ብሔራዊ መግባባት መጥፋቱን የግንባታው ጽ ቤት ገለጸ

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር ይሰራል፦ጽ/ቤቱ

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አስፈላጊነት ላይ ከህብረተሰቡ ጋር ብሄራዊ መግባባት መፍጠርና የተቀዛቀዘው የግድቡ ድጋፍ እንዲያድግ እንደሚሰራ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

ጽ/ቤቱ ‹‹የሀገራችን ሚዲያ ለሀገሩ ግድብ›› በሚል መሪ ቃል ከመገናኛ ብዙሀን ተቋማት ጋር የምክክር መድረክ አካሄዷል፡፡

መድረኩም የሚዲያ አካላት ለሀገር እድገትና ለትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ መፋጠን ባላቸው ሚና ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡

በቀጣይም የህዳሴው ግድብ ከነበረበት ችግር ተላቆ ህዝባዊ መግባባት እንዲፈጠር ምን ሊሰራ ይገባል፤ ለዚህም የሚዲያ አካላት ሚና ምን መሆን አለበት በሚሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

በውይይቱም ላይ ባለፉት ዓመታት የሚዲያ አካላት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ባበረከቱት አስተዋጽኦ ዙሪያ ሀሳብ ቀርቧል፡፡

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ችግር የነበረበት የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራም እየተስተካከለ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

አሁን ላይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሲቪል ስራ 83 በመቶ፤ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራው ደግሞ 25 በመቶ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የግድቡ የብረታ ብረት ስራም እየተፋጠነ እንደሆነ ነው የተገለፀው፡፡

የግድብ ግንባታ አሁን ላይ 66 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱን ከጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በቀጣይም በግድቡ ግንባታ አስፈላጊነት ዙሪያ ብሄራዊ መግባባትና ሀብት ለመፍጠር ከሚዲያ አካላትና ከህብረተሰቡ እንደሚሰራም ተገልጿል፡፡