አሁን ፍርድ ቤቶቻችን ላይ በተፅዕኖ የሚሆን ምንም ነገር የለም — ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ

ቢቢሲ

የኢትዮጵያ ህገ መንግሥት የቤተሰብ፣ የወንጀል፣ የጡረታና የዜግነት ህጎችን በተመለከተ ሴቶችን አግላይ በመሆኑ ሊሻሻል ይገባል በሚሉ ዘመቻዎች፤ የሴቶችን መዋቅራዊ ጥያቄ ወደፊት በማምጣትና ሀገራዊ አጀንዳ እንዲሆን ብዙ የሰሩት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነት ሆነው ከተሾሙ አምስት ወራትን አስቆጥረዋል። በነዚህ ወራት ምን አከናወኑ? ምን አይነት ተግዳሮቶችስ ገጠሟቸው? ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ

ቢቢሲ፦ከአምስት ወር ገደማ በፊት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነት ሆነው ሲሾሙ የገቧቸው የተለያዩ ቃል ኪዳኖች ነበሩ። በእነዚህ ወራት ምን ማሳካት ችለዋል? በዚህ ረገድስ ምን ያህል ተራምደዋል?

መዓዛ አሸናፊ እንግዲህ እኔ ስሾም ያልኩት አንድ ነገር በፍትሕ ስርዓቱ ላይ የሕዝብ አመኔታን መመለስ የሚል ነው። ምክንያቱም በተለያየ ምክንያት በተለይም በፍርድ ቤት ስርዓት ላይ ሕዝቡ አመኔታው ቀንሶ ነበር።

ፍርድ ቤት ስንል ዋናው ማዕከላዊ ሚና ያላቸው ዳኞች ናቸው፤ ከዳኞች ጋር እንዲሁም ደግሞ ከፍርድ ቤቱ ጋር ባለሞያዎች፥ ደጋፊ ሠራተኞች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች እያደረግን፥ ስልጠናዎችንም [እየሰጠን] ነው።

ይህንን በተመለከተ ዋናው መልዕክታችን ዳኞች በነፃነት፥ ሕጉን ብቻ ማዕከል አድርገው እንዲሰሩ ነው። ይሄንን ምናልባት እናንተም ዳኞችን ብትጠይቁ የምታገኙት መልስ በከፍተኛ ሁኔታ መነቃቃት እና በራስ መተማመን ፈጥሮብናል፤ እና በራሳችን ተማምነን እንድንሰራ ይሄ የተሰጠን አቅጣጫ ይጠቅመናል [የሚል ነው።] ይሄ ትልቅ እርምጃ ይመስለኛል። በሁለተኛ ደረጃ የተጠራቀሙ ጉዳዮች እየተለዩ እልባት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው።

በዚህ ረገድ በትጋት እየተሰራ ነው ያለው። የቆዩ መዝገቦች፥ የተከፈቱ መዝገቦች እያጠራን ነው ያለነው። ከዚያ ውጭ በዘላቂነት ለምንሰራቸው ደግሞ የማሻሻያ ለውጥ ስራ ጀምረናል። እርሱን ለመስራት ከፍተኛ ባለሞያዎች ያሉበት ጉባዔ ተቋቁሞ እነርሱም ደግሞ በሦስት ቡድን ራሳቸውን ከፍለው ስራ በመሰራት ላይ ነው የሚገኘው።

ለምሳሌ የዚያ የቡድኑ ሥራ ውጤት በሚመጣው መጋቢት 23 ለሕዝቡ ይፋ ይሆናል። ዳኞችን የሚያስተዳድረው አካል፥ የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ እንዲሻሻል፥ የማሻሻያ ኃሳብ ይዞ ቀርቧል ይሄ አማካሪ ቡድን። በዚያ ላይ ሕዝቡን እናወያያለን። ከፍርድ ቤት ውጭም እኛ የፍትሕ አካላት መሪ በመሆናችን፥ በዚያ ረገድም የፍትሕ ዘርፍ የማሻሻያ ለውጥ ፍኖተ ካርታ ረቂቁ ተዘጋጅቶ እርሱም ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ ዝግጅት ላይ ነን።

ቢቢሲ፦ብዙ ተግዳሮቶች እንደሚሩ መገመት ይቻላል። እርስዎን ያጋጠሙዎት ዋነኞቹ ማነቆዎች ምንድን ነበሩ?

መዓዛ አሸናፊዋና ችግር. . . . ዳኞችን የማጥራት (የቬቲንግ) ሥራ አስፈላጊ ነው፤ እንሰራለን። እስካሁን የነበሩት ዳኞች ሃቀኝነታቸው ምን ይመስላል? ችሎታቸው ምን ይመስላል? የሚለውን እንደገና የመፈተሽ ሥራ ይሰራል። ከዚያም በላይ ግን በጣም ከፍተኛ ችግር ሆኖ ያገኘሁት እኔ. . . ተቋሙ መሠረተ ልማት የለውም። ተረስቶ፥ በጣም ተዘንግቶ ወደ ጎን ተገፍቶ የቆየ ተቋም ነው ፍርድ ቤት። በዚያ ምክንያት ሰው ከሚገምተው በላይ ነው ችግር ያለው። ሌላው ቢቀር ዳኞች ችሎት የማስቻያ ቦታ የላቸውም፤ ዳኞች ቢሮ መቀመጫ የላቸውም። ከፍተኛ የግብዓት ችግር አለ። እና ከምንም በላይ እነዚህ የስርዓት እና የመሠረት ልማት ችግሮች እንደትልቅ ተግዳሮት ሆኖ ነው የማየው።

ቢቢሲ፦በሹመትዎ ዋዜማ ምን ጠብቀው ነበር? ሥራው ውስጥ ከገቡ በኋላስ ምን አጋጠመዎት? ከጥበቃዎ የተለየ ሆኖ የፈተነዎት ጉዳይ አለ?

መዓዛ አሸናፊእኔ በከፍተኛ ጉጉት እና በከፍተኛ ቁርጠኛነት ነው ወደዚህ ቦታ ኃላፊነቱን ወስጄ የመጣሁት፤ በሄድኩበት ቦታ ሁሉ ለውጥ እንደማመጣ ስለማውቅ። እና አንድ ቦታ ኃላፊነት ሲሰጠኝ ደግሞ መቶ ፐርሰንት ሳይሆን መቶ ሃያ ፐርሰንት ነው ራሴን ሰጥቼ የምሠራው።

በዚያ ጉዳይ ላይ ጥርጣሬ አልነበረኝም። ነገር ግን ምንድን ነው. . . ቅድም እንዳልኩት የፍርድ ቤት ችግሮችን [ለመፍታት] ተቋሙ ብዙ ግብዓቶችን ይጠይቃል፤ እየሰራን ነው። እኔ በዚህ በስድስት ወር ብዙ ሰርተናል ብየ ነው የማስበው።

ምናልባት ጊዜ ስለሌለን ወደዝርዝሩ አልሄድኩም እንጅ ዝርዝሮቹ ብዙ ናቸው። የሚፈለጉት ነገሮች ብዙ ናቸው፤ ከመዝገብ ብዛት ጀምሮ፥ የመዋቅር ችግር፥ የዳኞች ችሎታ ጉዳይ፥ የደጋፊ ሠራተኞች አቅም ጉዳይ፥ የሥራ አሰላለፍ ጉዳይ.. . . ብዙ ጉዳዮች ናቸው።

ነገር ግን የትኛው ነው ቶሎ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው? የትኛው ላይ ብናተኩር ነው ቶሎ ለውጥ ማምጣት የምንችለው? የሚለውን ቅደም ተከተል አስቀምጠን እየሠራን ነው። እና በሚመጣው አንድ ዓመት ጥሩ ውጤት እና ለውጥ በፍርድ ቤቶቻችን ላይ እንደሚታይ ምንም ጥርጣሬ የለኝም።

ከዚህ ጋር አያይዤ መናገር የምፈልገው፥ ከመንግስት ተቋማት ሌላ ብዙ አጋሮቻችን ሊረዱን ይፈልጋሉ። የመንግስት ተቋማት ነፃነታችንን በመጠበቅ፥ ነፃነታችንን በማክበር የሚያስደንቅ ዓይነት አካሄድ እያሳዩን ነው።

ከዚህም ውጭ የልማት አጋሮች የእኛን ስራ ለማገዝ ይመጣሉ። ከተለያዩ ኤምባሲዎችና ከተለያየ ቦታ ሥራችንን ለመደገፍ ዝግጁ ናቸው። በተወሰነ ደረጃም ደግሞ እኛም ፕሮጄክት እየቀረፅን በማስገባት እና በማስፀደቅ፥ በእነርሱ ድጋፍ የማሻሻያ ለውጥ ሥራችንን ለማንቀሳቀስ ትብብር ጀምረናል።

በጥቂቱ እንዳነሱልኝ ፍርድ ቤቶች ላይ ሲቀርብ የነበረው ትችት እና ነቀፌታ ከገለልተኛነት እና ከነፃነት ጋር የተገናኘ ነው። የፍርድ ቤቶችን ነፃነት በማስጠበቅ ረገድ ሥራ እየሠራችሁ እንደሆነ ነግረውኛል። ምን ያህል ተጉዛችኋል? ምን ያህልስ ይቀራችኋል?

የሚገርመው ነገር የፍርድ ቤት ነፃነት እኔ እዚህ ከተሾምኩ ቀን ጀምሮ የተጠበቀ ይመስለኛል። መምሰል ብቻ አይደለም። በተለያየ መንገድ. . . ኢመደበኛ የሆነ ውይይት ከዳኞች ጋር አደርጋለሁ፤ ‘ከበላይ ኃላፊዎቻችን ይሄ መልዕክት መተላለፉ ለእኛ ትልቅ ጉልበት ሰጥቶናል፥ ሥራ ይበዛብናል፥ መዝገብ ይበዛብናል፥ ሁኔታዎቻችን አልተሟሉልንም፤ ነገር ግን አሁን፥ ከበላይ አመራሮቻችን ነፃ ሆናችሁ ሥሩ፥ ምንም ጣልቃ ገብነት የለም መባሉ ለእኛ እንደ ትልቅ ኃይል ተጠቅመንበታል። ሌሎች ነገሮች እንዲሟሉ እየጠበቅን ነው፤ ነፃነታችንን በተመለከተ ግን በጣም ውስጣዊ ነፃነት ይሰማናል” የሚል መልስ ነው ከዳኞች የማገኘው።

ቢቢሲ፦በፍርድ ቤት ላይ የተያዙና ከፍተኛ አትኩሮትን የሳቡ ጉዳዮችን ላንሳልዎት፤ ከሙስና እና ከሰብዓዊ መብት ረገጣ ጋር በተያያዘ በታሰሩ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ። እነዚህን የፍርድ ቤት ጉዳዮች ፖለቲካዊ አንድምታ አላቸው የሚሉ ተችዎች አሉ። የቀጠሮዎችም መብዛት አብሮ ይተቻል። ለእነዚህ ትችቶች ምን ምላሽ አለዎት?

ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊየቀጠሮ መንዛዛት ሊኖር ይችላል። ሐኪም ስህተት ይሰራል። መሃንዲስ ስህትት ይሰራል። ዳኛም ስህተት ሊሠራ ይችላል። ነገር ግን ይሄ የቀጠሮ መራዘም ቢኖር፥ የተሳሳተ ውሳኔ ተሰጥቶብኛል የሚል ቡድን ሊኖር ይችላል፤ እነዚህ ሁሉ ግን [የሚሆኑት] ፍርድ ቤቱ ነፃነት ስለሌለው አይደለም። 

ይሄንን ነው ለሕዝቡ መልዕክት ማስተላለፍ የምፈልገው። የፍርድ ቤቶች፥ የዳኞች ነፃነት በምንም መልኩ ስለሚነካ አይደለም። በአሁኑ ሰዓት ፍርድ ቤቶቻችን ላይ በተፅዕኖ ምክንያት የሚሆን ምንም ነገር የለም። በሌላ በኩል ደግሞ ሕዝቡም ግንዛቤ ሊኖረው የሚገባው ምንድን ነው. . . ተከራካሪ ሁለት ነው።

እና የእነዚህ ሁለት ወገኖች ጥያቄ አቻችሎ አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ ሁለቱን አያስደስትም። ስለዚህ አንደኛው ቅሬታውን ይዞ አንደኛው አደባባይ ይወጣል፤ ሊናገር ይችላል። ነገር ግን እንዲያውም ከማንኛውም ሙያ በላይ የዳኞች ሥራ ነው ሊስተካከል የሚችለው።

ያም በምንድን ነው? በይግባኝ። ሁልጊዜም ይግባኝ አለ። ይግባኙ ለተከራካሪ ወገኖች እስከሰበር ድረስ ዕድል የሚሰጥ ነው። ስለዚህ ከነፃነት ጋር ወይ ከፖለቲካ ጋር በሚገናኝ ሁኔታ አይደለም።

ቢቢሲ፦አንዴ ላቋርጥዎትና. . . እነዚህ ጉዳዮች ግን ገና ውሳኔ አልተሰጠባቸውም።

ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊየጊዜ ቀጠሮን በተመለከተ እያንዳንዱ ዳኛ የራሱ አስተያየት አለው። አንድ መርማሪ ፖሊስ በጊዜ ምርምራ ጨርሶ፥ ለአቃቤ ሕግ ሰጥቶ፥ ፍርድ ካልተሰጠ ያ ጊዜ . . . ለምሳሌ በተባለው. . . የጉዳዩ ክብደት እና ቅለት ምን ይመስላል? ያ ሰው ቢለቀቅ ሊገኝ ይችላል ወይ? ብዙ ጉዳዮች አሉ እያንዳንዱ ዳኛ የሚመዝናቸው ከህጉ ውጭ።

ያንን ከግምት ውስጥ አስገብቶ፥ ‘የፖሊሶቻችን አቅም እኮ ደካማ ነው፤ የባለሞያዎቻችን ችሎታም ውሱን ነው፤ ስለዚህ ጊዜ ልስጣቸው’ ብሎ አንዱ ዳኛ ተለዋጭ ቀጠሮ ሊሰጥ ይችላል።

ባሉት የጊዜ ቀጠሮ ካላቀረቡ መለቀቅ አለበት ብሎ የሚወስንም ሊኖር ይችላል። ይሄ ከዳኛ ዳኛ የሚለይ ነው። ዞሮ ዞሮ እንዳልኩት ግን ይግባኝ ደግሞ መብት ስለሆነ፥ ይህ እየተስተካለለ ሊሄድ ይችላል።

ስራችን ፍፁም ነው ለማለት አልችልም። ከዳኝነት ሥራ ውስብስብነት የተነሳ፥ ካለንበት የሽግግር ሁኔታ የተነሳ፥ ካለንበት አቅም የተነሳ አሁንም የምንፈልገው ቦታ ላይ አልደረስንም።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE