“እስካሁን ሙሉ የሰውነት ክፍል ማግኘት እንደተቸገርን ለቤተሰብ እያስረዳን ነው” አቶ ተወልደ ገ/ማርያም

BBC Amharic : ባለፈው እሁድ ከቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ወደ ኬንያ ሲያቀና ቢሾፍቱ አቅራቢያ በተከሰከሰው አውሮፕላን የምርመራ ሂደትና ኢትዮጵያ በአውሮፕላኑ ላይ የጣለችውን የበረራ ዕገዳ በተመለከተ ቢቢሲ ከአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡

“እሁድ ዕለት እኔ አደጋ የደረሰበት ቦታ ስደርስ አውሮፕላኑ ሙሉ በሙሉ ከመሬት በታች ነበር፤ ከላይ ሲታይ ምንም ዓይነት የአውሮፕላን ማመልከቻ ነገር አልነበረም ” ይላሉ አቶ ተወልደ፡፡

እናም አስከሬኖቹንም ሆነ የአውሮፕላኑን ክፍሎች ለማግኘት ከመቆፈር ውጪ ምንም አማራጭ እንዳነበረ ይገልጻሉ፡፡

ተወልደ ገ/ማርያም

“እናቱ ስታየኝ ልጄ ያሬድ ይመጣል፤ እያለች ታለቅስ ነበር”- በናይሮቢ የካፒቴኑ ጸጉር አስተካካይ

“በጣም የሚሳዝነው ነገር እስካሁንም በጣም የተወሰኑትን የሰውነት ክፍሎች እንጂ ሙሉ የሰውነት ክፍል አላገኘንም፤ ይህ ደግሞ ለቀሪ ሥራዎችም ትልቅ ፈተና እንደሚሆንብን እንጠብቃለን ፤ ለሃዘንተኛ ቤተሰቦችም ይህን ችግር እያሰረዳናቸው ነው”

ዋና ስራ አስፈጻሚው የአውሮፕላን አደጋ ሊፈጠርባቸው የሚችሉባቸው ምክንያቶች በርካታ በመሆናቸው መላምቶችን ማስቀመጡ ተገቢ ባይሆንም አደጋው ከኢንዶኔዢያው የአውሮፕላን መከስከስ ጋር የሚመሳሰልባቸውን መንገዶች እንዳሉ ጠቅሰዋል.

“ሁለቱም ተመሳሳይ የአውሮፕላን ሥሪት ነበሩ፤ከመሬት ተነስተው ብዙም ሳይቆዩ ነው የተከሰከሱት፤የ በረራ ጊዜያቸው በጣም አጭር ነበረ፤ የእኛው አውሮፕላን በ6 ደቂቃ የኢንዶኔዥያው ደግሞ በ 8 ደቂቃ ነው የተከሰከሱት”

እናም እነዚህን መረጃዎች መነሻ በማድረግና ለመንገደኞች ህይወት ቅድሚያ ለመስጠት አውሮፕላኙን ከበረራ ማገድ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬም ስኬታማ ነው

“እኔ በግሌ እስካሁን ባስተዋልናቸው መመሳሰሎች ምክንያት እንደዚያ መሆን አለበት ብዬ ነው የማምነው፡፡ በቴክኖፖሎጂ የተራቀቁ ሃገራትም እኛን ተከትለው አውሮፕላኖቹን ከበረራ ለማገድ የወሰኑትም በቂ ምክንያት ቢኖራቸው ነው ፡፡እኛም ለደህንንት አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ በማሰብ ነው ወዲያውኑ አውሮፕላኑ ላይ አገዳ የጣልነው፡፡ ይህም ትክክለኛው ነገር እንደሆነ አስባሁ፡፡”

አቶ ተወልደ ይህ ለጉዳዩ ካላቸው ቅርበት የመነጨ ነው ባይ ናቸው፡፡

እርሳቸው ይህን ባሉበት ወቅት ቦይንግም ሆነ የአሜሪካ አቪየሽን ተቋም አውሮፕላኑ አስተማማኝ እንደነበር ገልፀው የነበረ ቢሆንም ኋላ ላይ ትናንት የአሜሪካ ሲቪል አቪየሽን ዛሬ ደግሞ ቦይንግ ኩባንያ ራሱ አውሮፕላኑ ከበረራ እንዲታገድ ወስነዋል።

“ቦይንግ የአውሮፕላኑ አምራች በመሆኑ ደህንነነቱ የተጠበቀ ነው እንደሚል ይጠበቃል፡፡ለአውሮፕላኑ ፈቃድ ለማገኘትም በተቆጣጣሪው አካል በኩል ማለፋቸው ስማይቀር ይህን ለማለት የራሳቸው ምክኒያ ሊኖራቸው ይችላል፤ ነገር ግን አዲስ አውሮፕላኖች፤ በአምስት ወራት ውስጥ፤ በተለያየ የዓለም ክፍል ውስጥ ፤ ሁለት ከፍተኛ አደጋዎች ማሰተናገዳቸውን ስናይ አውሮፕላኑን ለማገዳችን በጣም በቂ የሆነ ማብራሪያ መስጠት ይችላል”

ዋና ስራ አስፈጻሚሚው የኢንዶኔዥያው ላየን ኤይር አውሮፕላን ከተከሰከሰ በኋላ ቦይንግ አገዳውን ለመከላከል ያስችላል ያለውን መመሪያ ማስተለፉንና አየር መንገዱም ይህንኑ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረጉን ነው የገለፁት፡፡

“በዛ መሰረት አብራሪዎቻችንን አሰልጥነናል፤ መመሪያውንም በሁሉም የስልጠናና የስራ ማስኬጃዎቻችን ላይ አካተናል፤ ነገር ግን ይህ በቂ የነበረ አይመስልም”

አየር መንገዱ የተከሰከሰውን የአውሮፕላን ዓይነት ለመግዛት እቅድ እንደነበረው የገለጹት አቶ ተወለደ አሁን ግን የአደጋ መርማሪ ቡድኑ ሪፖርት እስሚወጣ ድረስ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

“አሁን መልስ ያላገኘንላቸው በጣም ብዙ ጥያቄዎች አሉን ፤ ነገር ግን ምላሽ ሊያገኙ የሚችሉት ከምርመራው ብቻ ነው ። እሰከዚያም ቢሆን ለቅድመ ጥንቃቄ ሲባል አውሮፕላኑ ላይ እገዳ እንዲጣል እመክራሁ”