ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚያደርግ የፈረንሳይ ጦር በኢትዮጵያ ሊሰፍር ነው ።

Image result for france armyለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ማክሰኞ መጋቢት 3 ቀን 2011 ዓ.ም. አዲስ አበባ የገቡት የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ ‹‹በሥልጠና ላይ ያተኮረ ሕጋዊ የፈረንሣይ ጦር ወደ ኢትዮጵያ እንልካለን፤›› ሲሉ አስታወቁ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ይኼን ያሉት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በመሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

‹‹በመከላከያ ያለን ትብብር እንደሚታወቀው ፈረንሣይ በምሥራቅ አፍሪካ ያላት አስተዋጽኦ ጂቡቲ ላይ ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንት ማክሮን፣ ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረገው የመከላከያ ትብብር ፈረንሣይ በምሥራቅ አፍሪካ የሚኖራትን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ያግዛል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በፈረንሣይ ትምህርት ቤቶች ሥልጠና እንዲያገኙ፣ እንዳስፈላጊነቱ ፈረንሣይ በኢትዮጵያ ያላትን ሚና ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በበኩላቸው ከፈረንሣይ ጋር የሚኖረው ትብብር ጊዜያዊ ሳይሆን፣ ለ100 እና 200 ዓመታት የሚዘልቅ እንዲሆን እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ከፈረንሣይ ጋር ያለን ወዳጅነት እስከ ኑክሌር ማብላያ ድረስ ይዘልቃል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከመከላከያ ዘርፍ ትብብር በተጨማሪም በኢኮኖሚ ዘርፍ ትብብር ለማድረግ ስምምነት የተፈረመ ሲሆን፣ ፈረንሣይ ለኢትዮጵያ የ85 ሚሊዮን ዩሮ በረዥም ጊዜ የሚከፈል ብድርና የ15 ሚሊዮን ዩሮ የልማት ድጋፍ እንዳደረገች ተገልጿል፡፡

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በተመለከተ ሥፍራውን ሄደው በመጎብኘታቸው የሕዝቡን መንፈሳዊነት ዓይተው እንደተደሰቱ የገለጹት ማክሮን፣ ፈረንሣይ ለቅርሶቹ ጥበቃ የገንዘብና የሙያ ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል፡፡

Reporter Amharic


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE