በጌዲኦ ዞን ለሚገኙ 172 ሺህ ተፈናቃይ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ ነው ተባለ

ጌዲኦ ዞን ለሚገኙ 172 ሺህ ተፈናቃይ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

ለማስታወስ ያህል — ዜናው የዛሬ ነው ፎቶው ግን ባለፈው አመት ነሃሴ ወር የተነሳ ነው።

የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ ገዙ አሰፋ በሰጡት መግለጫ ከእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመሆን ችግሩን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመቅረፍ የሚያስችል ስራ በማከናወን ላይ መሆኑንም ገልጿል።

አስተዳዳሪው በምዕራብ ጉጅ ዞን መንግስት በአካባቢው ታጣቂዎች ላይ በወሰደው እርምጃ ስጋት የገባቸው እና በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው በገደብ ወረዳ ጎቲቲ ቀበሌ ከ37 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በ6 መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በጎቲቲ የተጠለሉትን ጨምሮ ባለፈው አመት በተነሳው ግጭት ተፈናቅለው ያልተመለሱና በተለያዩ ጊዜያት መተው በዘመዶቻቸው ቤትና በተለያየ ሁኔታ የተጠለሉ በዞኑ ከ172 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ዞኑ ምግብ ነክ ድጋፍ ለማድረስ ባደረገው ጥረት 25 ሺህ ኪሎግራም አልሚ ምግብና 3 ሺህ ኪሎ ግራም ዱቄት በጎቲቲ ለተጠለሉ ተፈናቃዮች መሰራጨቱን ተናግረዋል።

ከአለም ምግብ ድርጅት ጋር በመቀናጀትም ለቀጣይ አንድ ወራት ምግብ ለማድረስ ከስምምነት የተደረሰ ሲሆን ሌሎች የእርዳታ ድርጅቶችም ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ወደ አካባቢው ማድረስ መጀመራቸውን አስረድተዋል።

ችግሩንም በዘላቂነት ለመፍታት ከፌዴራልና ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በጋራ እየተሰራ እንዳለም አስተዳዳሪው መናገራቸውን ከዞኑ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE