«በጠበቆቻችን ላይ ዛቻ እየደረሰ ነው» አቶ በረከት ስምዖን

እነ አቶ በረከት «በጠበቆቻችን ላይ ዛቻ እየደረሰባቸው ነው» ሲሉ ለባሕር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ተናገሩ። ባለፉት 3 የፍርድ ቤት የቀጠሮ ክርክሮች በራሳቸው ሲከራከሩ የቆዩት ተጠርጣሪዎች ትናንት ሁለት ጠበቆችን አቁመው ተከራክረው ነበር። ፍርድ ቤቱ ትናንት በይደር ያቆየውን የምርመራ ጉዳይ ክርክር ዛሬ ተመልክቶ ውሳኔ ሰጥቷል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች ትናንት ምርመራው በቂ በመሆኑ እየተጠየቀ ያለው የጊዜ ቀጠሮ ተጠርጣሪዎችን ለማጉላላት ሆን ተብሎ የሚደረግ ሥራ መሆኑን ጠቅሰው ደንበኞቻቸው በዋስ ተለቅቀው ጉዳያቸውን ከውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀው ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ በዛሬው ውሎ፦ የአማራ ክልል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን በጠየቀው መሰረት ቀረኝ የሚለውን ምርመራ አጠናቅቆ እንዲቀርብ ለመጋቢት 11/2011 ቀጥሯል፡፡

ከውሳኔ በኋላ አቶ በረከት ለመናገር እንዲፈቀድላቸው ችሎቱን የጠየቁ ቢሆንም ፈቃድ አላገኙም፣ ይሁን እንጂ «በጠበቆቻችን ላይ ዛቻ ደርሶባቸዋል፣ እኛም እንደ ጦር ምርኮኛ እተቆጠርን ነው» ሲሉ በስሜት መናገራቸውን የፍርድ ውሎውን የታደመው የባሕር ዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን ገልጧል። ፍርድ ቤቱ አሉ የሚባሉ ችግሮችንና ተጠርጣሪዎች ቅሬታዎቻቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ አሳስቧል።


► መረጃ ፎረም - JOIN US
► MEREJA TV YOUTUBE CHANNEL - SUBSCRIBE