Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
Za-Ilmaknun
Member
Posts: 4095
Joined: 15 Jun 2018, 17:40

አባ ገዳ ጎበና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባል የሆነው ልጃቸው መገደሉን ከማኅበራዊ ሚዲያ መስማታቸውን ተናገሩ

Post by Za-Ilmaknun » 22 Apr 2024, 12:40

የቱለማ አባ ገዳ የሆኑት አባ ገዳ ጎበና ሆላ ኢሬሶ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባል የሆነው ልጃቸው መገደሉን ከማኅበራዊ ሚዲያ መስማታቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከአንድ ሳምንት በፊት በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን ኮሚዩኒኬሽን መንግሥት ‘ሸኔ’ የሚለው ቡድን አባል ነው ያለው የአባ ገዳ ጎበና ልጅ “ሰላማዊ ሰዎችን ለመግደል ሲንቀሳቀስ እርምጃ ተወስዶበታል” ብሎ ነበር።

የቱለማ አባገዳ እና የኦሮሞ አባገዳዎች ኅብረት ፀሐፊ የሆኑት አባ ገዳ ጎበና ሆላ፣ ፎሌ ጎበና የሚባለው ልጃቸውን መገደል የሰሙት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከሚሠራጨው ወሬ መሆኑን እና አስካሁን ምንም ማረጋገጫ እንዳላገኙ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግረዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት አባ ገዳ ጎበና ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ቤታቸው ላይ ብርበራ በተደረገበት ወቅት ከወላጅ አባታቸው የወረሱት የጦር መሳሪያ መወሰዱን እና ክስተቱን ተከትሎ በቤተሰብ አባላት ላይ ከፍተኛ መደናገጥ መፈጠሩን ተናግረው ነበር።

አባ ገዳ ጎበና ከቀድሞ የቱለማ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ መስከረም 20/2011 ዓ.ም. በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ የሆነውን ባሕላዊ ሥልጣንን መረከባቸው ይታወሳል።

https://www.bbc.com/amharic/articles/c72p687d4ywo