Ethiopian News, Current Affairs and Opinion Forum
sarcasm
Senior Member
Posts: 10186
Joined: 23 Feb 2013, 20:08

"ከምንም በላይ ግጭትንና ጦርነትን የሚያስቀር የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ አተኩሮ መሥራት ከሁሉም ይጠበቃል" የአማራ ክልል መንግሥት

Post by sarcasm » 20 Mar 2022, 10:55

አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል በዜጎች መፈናቀልና ግጭት ሳቢያ የሚያጋጥሙ ማህበራዊ ቀውስና ጫናን ለመቀነስ ከጎረቤት ክልሎች ጋር በጋራ እንደሚሠራ ክልሉ አስታወቀ።

Ethiopian Press Agency /የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/


የአማራ ክልል መንግሥት የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በዜጎች መፈናቀልና አሸባሪው ሕወሓት ባደረሰው ወረራ ምክንያት ብዙዎች ለችግር ተጋልጠዋል። በዚህ ሳቢያ በክልሉ እያጋጠመ ያለውን የማህበራዊ ቀውስ ችግር ለመቀነስና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከጎረቤት ክልሎች ጋር ይሠራል።

ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጫና እንዳይኖር ቀጣናውን ሠላም ማድረግ ይገባል ያሉት አቶ ግዛቸው፤ አሁን ላይ እየታየ ያለውን የማህበራዊ ቀውስ ጫና ለመቀነስ፣ ከጎረቤት ክልሎች ጋር ሠላምን የጋራ አጀንዳ አድርጎ አንደሚሠራ ተናግረዋል። ለሰላም መደፍረስና ለጦርነት የሚዳርጉ እንዲሁም ለዜጎች መፈናቀል መነሻ የሆኑ ጉዳዮችን በጋራ ምክክር መፍታት ትልቁ መፍትሄ እንደሆነ አመላክተዋል።

አቶ ግዛቸው፤ ቀውሱ በጋራ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አመለካከት በመያዝ ሊፈታ እንደሚችል ገልጸው፤ ከምንም በላይ ግጭትንና ጦርነትን የሚያስቀር የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ አተኩሮ መሥራት ከሁሉም ይጠበቃል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል ቀውሱ እንዳይከሰትና ጉልበተኛ እንዳያፈናቅልና እንዳይገድል ለማድረግ ራስን ማዘጋጀትና ማደራጀት እንደሚያስፈልግም አቶ ግዛቸው ጠቅሰዋል። ይህ ሲባል በጦር በመሣሪያ ብቻ ሳይሆን «ምን ሲሆን ነው ችግሩ የሚፈታው?» በሚል እሳቤ ራስን አደራጅቶ፤ መጠበቅ ተገቢ ነው ብለዋል። በሚያፈናቅለውና መጥፎ ሀሳብ ይዞ በሚሠራው ኃይል በኩል ያለውን ሀሳብ ለማሸነፍ የመጀመሪያው ጉዳይ በሀሳብ አሸንፎና በልጦ መገኘት ሲሆን ሰውንም በዚህ ዙሪያ ለማሰለፍ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኢኮኖሚ አቅምን መፍጠር፣ የጸጥታ ተቋምን ማደራጀት፣ ተቋማዊ ሥርዓት የሚያስከብሩ አካላትን በሚገባ በሥነምግባርና በአመለካከት ማነጽ እንደሚገባ ተናግረዋል። ይህን ለማድረግም በትብብርና በወንድማማችነት መንፈስ ይሠራል ብለዋል።

ችግሮች ሲያጋጥሙ መንግሥትና የጸጥታ አካላት ብቻቸውን የሚፈቱት ባለመሆኑ ሁሉም አካል የመፍትሄ ባለቤት እንዲሆንም ጠይቀዋል። በአነስተኛ ኑሮ ከሚኖረው ጀምሮ እስከ ትልልቅ ባለሀብት ያለው፣ ከአርሶ አደር እስከ ምሁራን ያሉት፣ ዳያስፖራውና የሃይማኖት አባቶች ሚናቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የጸጥታ አካላትም በዲስፕሊን በመመራትና ለሕዝብ ጥቅም ሌት ከቀን በመሥራት ራስን አሳልፎ መሥራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ደግሞ በመንግሥትም በኩል ችግር የሚፈጥሩ አካላትን ፈጥኖ ለሕግ የማቅረብ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግና አጠቃላይ ዘላቂ በሆነ መንገድ ችግሩን ለመፍታት በዚህ ደረጃ እየተሠራ እንዳለ አመላክተዋል።

አቶ ግዛቸው አክለውም ችግሮች በፌስ ቡክና በሚዲያ ጋጋታ አይፈቱም ብለዋል። ከአክቲቪዝም ጋር ተያይዞ የዲጂታል ሚዲያው የእድገት ደረጃ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን እያባባሰ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ዲጂታል ሚዲያው ጠቃሚ ዘርፍ ቢሆንም፤ አጠቃቀሙ ላይ ግን ክፍተቶች እንዳሉ ነው የገለጹት። ችግሮች የሚፈቱበትን ነገር እያወሳሰበ ቁርሾ እየጨመረ የማስኬድ አዝማሚያ እንደሚንጸባረቅበትም ገልጸዋል። በመሆኑም በዚህ ዙሪያ የተጠያቂነት አሠራር ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም

https://www.press.et/ama/?p=69110